የወላይታ ዞን የተቃዋሚ ድርጅት አባላት ራሳቸውን ከምርጫው ሊያገሉ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ

ሚያዝያ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው በወላይታ ዞን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት ዕጩዎችን ያቀረቡ 8 የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዞኑ እየደረሰባቸው የሚገኘው አፈና እና በደል መፍትሄ ካልተሰጠው ራሳቸውን  ግንቦት 2007 ዓ.ም ምርጫ ሊያገሉ እንደሚችሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዞኑ ምርጫ ማስተባበሪያ፣ ለምርጫ ቦርድና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ባስገቡት ደብዳቤ ገልጻዋል።

ማስጠንቀቂያውን የጻፉት ድርጅቶች ሰማያዊ፣ የኢትዮጵያ ፍትሕና ዴሞክራሲ ሃይሎች ግንባር ፣ የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት

መድረክ  እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ  ናቸው፡፡

ፓርቲዎቹ ለምርጫ ምቹ የሆነ አጋጣሚ እንዳለ በሚዲያ የሚገለፀው ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል።  በየጊዜው አቤቱታቸውን ለምርጫ ክልሎችና ለጋራ ምክርቤት ቢያቀርቡም ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኙና በአባላቶቻቸው ላይ የሚፈፀመው በደል ከአቅማቸው በላይ

መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹የወረዳና የዞን የምርጫ አስተባባሪዎች የገዥውን ፓርቲ ድምጽ ከመስማት በስተቀር ምንም አይነት ውሳኔ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡›› ያሉት ፓርቲዎች፣ በዚህም ምክንያት ምህዳሩ እጅግ መጥበቡንና ከችግር ላይ ችግር እየተደራረበ በመምጣቱ ከፍተኛ አደጋ ላይ መሆናቸውን በደብዳቤው ገልጸዋል፡፡