በአማራ ክልል የሚገኙ የቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች ኪሳራ እየደረሰባቸው መሆኑን ገለጹ፡፡

ሚያዝያ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጎንደር ከተማ ሰሞኑን በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙ የቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች እንደተናገሩት፤ ባለድርሻ አካላት ስራቸውን በአግባቡ ባለመስራታቸው ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በቆዳ ፋብሪካ ዘርፍ የተሰማሩ ጥቂት ባለሃብቶችን ለመደገፍ በሚል ሰበብ  የጥሬ ቆዳና ሌጦ ዋጋን በዝቅተኛ ዋጋ እንዲቀርብ መመሪያ በማውጣታቸው በላተኛ ህብረተሰቡና አቅራቢ ነጋዴዎች መጠቀም የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ነጋዴዎቹ በቅሬታ ገልጸዋል፡፡

ቅሬታቸውን የሚገልጹት ነጋዴዎች የፍየል ቆዳ ዋጋ ሶስት ብር መሆኑ በላተኛው ወደ ገበያ ከማምጣት ይልቅ በቤቱ በማዘጋጀት ለመቀመጫነት ለመጠቀም መገደዱ በዘርፉ ያለውን እንቅስቃሴ እየጎዳው በመሆኑ ነጋዴዎች ምንም ሳይሳሩ ግብር ከመክፈል ስራውን ማቆምን እንደሚመርጡ በምሬት ተናግረዋል፡፡

“ ህገወጥ ነጋዴዎች ከተለያዩ የመንግስት አመራሮች ጋር በመመሳጠር እጅና ጓንት በመሆን ፈቃድ ለማውጣት መሟላት ያለባቸውን መስፈርት ሳያሟሉ በተጭበረበረ መንገድ  ፈቃድ በማግኘት ፤ ያለአግባብ ጥቅም ማግኘት እንዲቻል የማድረግ ስራ በየወረዳው መሰራቱ በዘርፉ ያሉ ነጋዴዎች እንዲዳከሙና ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ አድርጓል” ሲሉ ባለሙያዎች ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡   “የንግድና ፖሊስ ጽህፈት ቤቶች እየተባበሩን አይደሉም፡፡በተለይ በወረዳ ላይ ያሉ ንግድ ና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ስራ እየሰራ አይደለም፡፡ ”የሚሉት ሌላው ባለሙያ፣ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ከተለያዩ ፋብሪካዎች ጋር ውል በመያዝ ቆዳውን ቢያስረክቡም ገንዘባቸውን እስከ አንድ አመት ድርስ ሳያገኙ እስካሁን መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው አክለውም “ በንግድ ዙሪያ የሚሰሩ በወረዳ አካባቢ ያሉ ባለሙያዎች አዋጅና መመሪያዎችን ስለማያውቁ ተገቢው ስልጠና ሊሰጣቸው ይገባል ” በማለት ገልጸዋል፡፡-ኢትዮጵያ በአፍሪካ የእንስሳት ቁጥር በአንደኝነት ስትጠቀስ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ግን እጅግ አነስተኛ ነው።