የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር- የመንግስት ሚዲያዎችን ተቸ

ጥር ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቲቪ(ኢቢሲ) ፣ራዲዮ ፋና እና ሌሎች የመንግስት ሚዲያዎች በምርጫው ዙሪያ ጠንካራ ስራ አልሰሩም ሲል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ተቸ።

የመንግስትና የድርጅት ሚዲያዎች  ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ  ለተፎካሪ ፓርቲዎች በተሰጣቸው አጀንዳ ዙሪያ ብልጫ ያለው ስራ  አልሰሩም ሲል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር -የኢትዩጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬትን ወቀሰ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ -ለኢቢሲ  ባስተላለፈው የደብዳቤ ትእዛዝ በቀጣይ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ  ብዙሀን መገናኛዎች ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ በምርጫ  ለኢህአዴግ ድጋፍ የሚያስገኙ ፕሮግራሞችንና ዶክመንተሪዎችን ያለማሳለስ እንዲሰሩ ከማስጠንቀቂያ ጋር እንዲነገራቸው አሳስቧል።
ሚዲያዎቹ በተለይ የደጋፊዎችን ድምጽ በማሰባሰብና የድርጅቱን ፖሊሲና ስትራቴጂ በመከተል  በጽሁፎችና በፕሮግራሞች ብቃት ያላቸውን ስራዎች  በተከታታይ እንዲሰሩ  እንዲደረግ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር አስጠንቅቋል።

እስካሁን ፋና ኮርፖሬትንና ኢቢሲን  ጨምሮ በክልል ያሉት ብዙሀን መገናኛዎች አማራጭ ፖሊሲዎች ላይ የአመለካከት ልዩነት እንዳለ ለማሳየት  አንዳንድ ስራዎችን ቢሰሩም፤ የተሰሩት ስራዎች ጠንካራ አደሉም ተብለው ተተችተዋል፡፡