በመላ ሀገሪቱ ዜጎች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ እየተገደዱ ነው።

ጥር ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የባህርዳር፣የአዲስ አበባ፣ የአምቦ፣ የጅማ፣የድብረማርቆስ እና የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ለኢሳት ወኪሎች እንደተናገሩት  በየቤቱ እየዞሩ  የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ በሚቀሰቅሱ ካድሬዎች ከመረበሻቸውም በላይ  የምርጫ ካርድ ካላወጡ ስለሚጠብቃቸው ቅጣት  ዛቻና ማስፈራሪያ እየተፈጸመባቸው ይገኛል።

ሲጀመር ምርጫ መኖሩ በየቀኑ በራዲዮና በቴሌቪዥን እየተለፈፈ ባለበት ሁኔታ  በር እያንኳኩ ምርጫ ካርድ ውሰዱ ብሎ መቀስቀሱ አስፈላጊ አልነበረም ያሉት የባህርዳር ነዋሪዎች፤ ቅስቀሳው ግዴታ አስፈላሰጊ ነው ከተባለም<<ካርድ አልወስድም!አልመርጥም!>> ያለን ዜጋ ማሰፈራራቱን ምን አመጣው?”ሲሉ ጠይቀዋል። መምረጥም፣ አለመምረጥም  የራሳችን መብት እስከሆነ ድረስ በካድሬዎች ልንረበሽና ልንገደድ አይገባም የሚሉት የየከተሞቹ ነዋሪዎች፤ << እንድንመርጥ አፈ-ሚዝ ከተደቀነብን የምንመርጠውን እናውቃለን>> ሲሉ ተናግረዋል።