የኬንያ ፕሬዝዳንት ቃለ መሃላ ፈጸሙ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 19/2010) የኬንያ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ኡሁሩ ኬንያታ ዛሬ ቃለ መሃላ ፈጸሙ።

ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ ግን ኬንያታ የተመረጡት ዝቅተኛ ቁጥር ባላቸው ድምጽ ሰጪዎች በመሆኑ በሚቀጥለው ወር ራሳቸው የፕሬዝዳንትነት ቃለመሃላ እንደሚፈጽሙ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

ከሁለት አጨቃጫቂ ምርጫዎች በኋላ የኬንያ ፕሬዝዳንትነትን መንበር ለሁለተኛ ጊዜ የተቆጣጠሩት ኡሁሩ ኬንያታ ቃለ መሃላቸውን ሲፈጽሙ ተቃዋሚዎች በስነስርአቱ ላይ አለመታደማቸው ታውቋል።

ኬንያታ በንግግራቸው ሁሉን አቀፍ ስሜት ለመፍጠር በተቃዋሚዎች የሚነሱ አንዳንድ ሃሳቦችን እቀበላለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።

የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ በበኩላቸው በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ወር ጉባኤ በመጥራት የፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ መናገራቸው ግርታን ፈጥሯል።

ኦዲንጋ ባላፈው ወር በድጋሚ ከተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል።

ባለፈው ነሀሴ በኬንያ የተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማጭበርበር ተፈጽሞበታል በሚል ነበር ባለፈው ወር በድጋሚ የተካሄደው።

በድጋሚው ምርጫ መምረጥ ከሚችለው 39 በመቶ ያህሉ ብቻ ድምጽ ሲሰጥ ኬንያታ ከዚህ ውስጥ 98 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።

በናይሮቢ ካሳራኒ ስታዲየም ከታደሙት የውጭ ሀገራት መሪዎች መካከል የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ ይገኙበታል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናትንያሁ በስነ ስርአቱ ላይ ባይገኙም በቤተመንግስቱ በሚደረገው ስነስርአት ላይ እንደሚገኙ ይጠበቃል።

የተቃዋሚ ፓርቲው ደጋፊዎች ከፖሊስ ጋር የተጋጩ ሲሆን ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱን ቢቢሲ ዘግቧል።

የኬንያው ስታር ጋዜጣ ግን ፖሊስ የኦዲንጋን ደጋፊዎች ለመበተን ባደርገው ሙከራ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አስፍሯል።

ዱንሆልም በተባለው የመዲናይቱ ክፍል የተቃዋሚ ደጋፊዎች ጎማ በማቃጠል መንገድ የዘጉ ሲሆን ራይላ ፕሬዝዳንት ካልሆኑ ሰላም የለም ሲሉም ተደምጠዋል።

አንዱ በባላ ላይ ድንጋይ ሊወረውር የተዘጋጀ ተቃዋሚ ለቢቢሲ እንደተናገረው ለኡሁሩ ኬንያታ ፕሬዝዳንትነት እውቅና እንደማይሰጡ ተናግረዋል።

ተቃዋሚው ኦዲንጋ ለደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ ኡሁሩ ኬንያታ በጣም ትንሽ በሆኑ ድምጽ ሰጪዎች ስለተመረጡ በፈረንጆቹ ታህሳስ 12 ራሳቸው የፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ ተናግረዋል።