የኢሳት 7ኛ አመት በኮሎምቦስ ኦሃዩ ተከበረ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 19/2010)የኢሳት 7ኛ አመት በኮሎምቦስ ኦሃዩ በድምቀት ተከበረ።

በበአሉ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልና የኢሳት ድርሻ በሚል ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

ቅዳሜ ህዳር 25/2017 በኦሃዩ በተከበረው የኢሳት 7ኛ አመት ላይ ከኦሃዩና አካባቢዋ፣ከሴንሴናቲ፣ከዴይተን፣ክሊቭላንድና ኢንዲያና ግዛት የመጡ የኢሳት ደጋፊዎች ተሳትፈዋል።

በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ኮመዲያን ክበበው ገዳና የኢሳት ባልደረባው አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ሲሆኑ ኮመዲያን ክበበው ገዳ ለዝግጅቱ ልዩ ድምቀት ሰጥቶት ነበር።

አቶ ኤርሚያስ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልና የኢሳት ድርሻ” በሚል ርዕስ ገለጻ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነትና ዲሞክራሲ ትግል ውስጥ ኢሳት እያበረከተ ያለውን አስተዋጾ አብራርተዋል።

የአገዛዙ ሃይሎች ኢሳትን ከሳተላይት ለማውረድ ከ27 ጊዜ በላይ የሞከሩት በዚህ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

በቅርቡም የሕወሃት አባላት በሆኑት ጄኔራል ሳሞራ የኑስና የደህንነት ሃላፊው ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ባወጣው ሪፖርት “የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተከፍቶብናል”በሚል ኢሳት ምን ያህል እንዳስጨነቃቸው ያመላክታል ብለዋል።

ከገለጻው በኋላም የጨረታና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ተካሂደዋል።

ከጨረታው መጠናቀቅ በኋላ የበአሉ ተካፋዮች ለኢሳት አዲሱ ስቱዲዮ ሊያገለግል የሚችል ተጨማሪ ቪዲዮ ካሜራ መግዣ የሚሆን ከ3 ሺ ዶላር በላይ አዋጥተዋል።

ካሜራውን ገዝተው ለማስረከብም ቃል ገብተዋል።

በቀጣይም የኢሳት ሰባተኛ አመት ክብረ በአል ቅዳሜ ዴሴምበር 2 በቦስተን ማሳቹሴትና ሂውስተን እንደሚካሄድ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።