የኬንያ ልዩ ተጠባባቂ ሀይል ከኢትዮጵያ ሰርገው በገቡ ታጣቂ ሀይሎች ላይ ዛሬ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ይፋ አደረገ

ነሃሴ ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የገቡ ታጣቂ ሀይሎች አራት የኬንያ ተጠባባቂ ፓሊሶችንና ስድስት አሳ አጥማጆችን በመግደላቸው በሁለቱ ድንበር አካባቢ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡

የኬንያና የኢትዮጵያ የፀጥታ እና ደህንነት ባለስልጣናት ጉዳዩን አስመልክቶ በመወያየት ላይ ሲሆኑ ጉዳዩ ያሳሰበው የኬንያ ተጠባባቂ ልዩ ሀይል ዛሬ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በገቡት ታጣቂ ሀይሎ ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የገቡት ታጣቂዎች በቱርካና ሀይቅ ዙሪያ ሶስት ትናንሽ ደሴቶችን ይዘው የሚገኙ ሲሆን የኬንያ ልዩ ሀይሎችም ታጣቂዎቹን ከያዙት ቦታ ለማስለቀቅ ከፖሊስ ጋር በመተባበር ጥቃት በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ የኬንያው ዘ ስታር ጋዜጣ ባለስልጣናቱን በመጥቀስ ዘግቧል፡፡

150 ልዩ የኬንያ ተጣባባቂ ሀይሎችን ያካተተው የኬንያ እርምጃ በሁለቱ አዋሳኝ ድንበር ላይ በምትገኘው ቶዶንያንግ ላይ እየተካሄደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኬንያ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ታጣቂ ሀይሎች ከያዙት አካባቢ ለማስወጣት የፀጥታ ሀይሎች እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆናቸውን የዘመቻው አስተባባሪ የሆኑት ኤሪክ ዋንዬንዬ ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሰርገው የገቡት ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ያዋሏቸውን በርካታ ጀልባዎች እንዲመልሱም ቀነ ገደብ እንደተሰጣቸው የተናገሩት ኤሪክ ታጣቂዎቹ በወሰዱት እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኬንያ ዜጎች ከቤታቸው መሰደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

እየተካሄደ ያለውን ጥቃት ተከትሎ ስድስት ሰዎች በቱርካና ሀይቅ አካባቢ የገቡበት እንዳልታወቀ የጥቃቱን እርምጃ የሚያስተባብሩት ኤሪክ አክለው ገልጸዋል፡፡

የቱርካና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ጆን ሙንየስ ኬንያ ሰራዊቷን በሁለቱ ሀገራት ድንበር ዙሪያ እንድታሰፍር ጠይቀዋል፡፡

ኬንያውያን መገደላቸው በጣም አስቆጥቶናል መንግስታችን ተገቢ የሆነ እርምጃን መውሰድ አለበት በማለት ሙንየስ ከኤልዶሬት ከተማ ተናግረዋል፡፡

በትላንትናው እለት ከኬንያ ልዩ ተጠባባቂ ሀይሎች በተጨማሪ በርካታ የፀጥታና ደህንነት ባለሙያዎች በሁለቱ ሀገራት ድንበር ዙሪያ እንዲሰፍሩ መደረጉን የምክር ቤቱ አባል ተናግረው፤ የኬንያ የሀገር ውስጥ ካቢኔት ፀሀፊ የሆኑትን ጆሴፍ ኦሌ መንግስታቸው ሰራዊቱን በአስቸኳይ በድንበር ዙሪያ እንዲያሰፍር ጠይቀዋል፡፡