በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በመንግስት ተወካዮች ‹በሀይማኖት መቻቻል› ዙሪያ የተጠራ የውይይት መድረክ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው

ነሃሴ ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዛሬ በአዲስ አበባ ወረዳ ሶስት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ድላችን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመንግስት ተወካዮች ‹በሀይማኖት መቻቻል› ዙሪያ የተጠራ የውይይት መድረክ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው ተሰማ፡፡

በስብሰባው ላይ የታደሙት የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች የመንግስት ተወካዮች እየተካሄደ ያለውን የሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ከአክራሪነትና አሸባሪነት ጋር ለማያያዝ ያደረጉትን ማብራሪያ አንድ አይነት አቋም በመያዝ መቃወማቸውን ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች አመለከቱ፡፡

የአይን እማኞች ሁኔታውን አስመልክቶ ለኢሳት እንደተናገሩት ከሆነ የመንግስት ተወካዮች የያዙትን የመወያያ አጀንዳ ‹በቴሌቪዥን ሰልችቶናል› በማለት ተሳታፊዎቹ በጋራ ተቃውመውታል፡፡

በስብሰባው ላይ የተሳተፉት የሁለቱ ሀይማኖቶች ተወካዮች መንግስት በሙስሊሙ የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ እየወሰደ  ያለውን የሀይል እርምጃ ቆም ብሎ እንዲያጤን የጠየቁ ሲሆን አክራሪነትና ሽብርተኝነት የሚለው መወያያ ስጋታቸው አለመሆኑን መግለጻቸውን የአይን እማኞች ለኢሳት ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት የኢድ አልፈጥር በአል አከባበር ወቅት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ታስረው የነበሩ 2ሺህ ሰዎች አሁንም ድረስ በቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፖሊስ በበኩሉ ቁጥራቸውን ሊገልጽ ያልፈቀደ ሰዎች የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው መፍቀዱን ገልጿል፡፡

ፖሊስ ጥቂት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል በማለት በወቅቱ የተናገረ ቢሆንም፤ የተለያዩ ተቋማት አዳራሾችና ትምህርት ቤቶች ስልፈኞችን ለማቆያነት ውለው እንደነበር በመንግስት የመገናኛ ብዙሀን በኩል ይፋ አድርጓል፡፡

አምኒስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌላ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መንግስት በሙስሊም መብት ጠያቂዎች ላይ የሚያካሂደውን እስራትና እንግልት እንዲያቆም በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡