የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳንና የኢትዮጵያ የጋራ ፕሮጀክት

የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ በጣምራ  እጅግ ታላቅ የሆነ ወደብና የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ ላማካሄድ የመሰረት ድንጋይ አኖሩ።

ቢቢሲ እንደዘገበው ይህ በ አፍሪካ ደረጃ ታላቅ ነው የሚባለው ፕሮጀክት  23 ቢሊዮን ዶላር ወይም በወቅቱ ምንዛሬ መሰረት ወደ 400 ቢሊዮን የሚደርስ የኢትዮጵያ ብር ይፈጃል።

ይሁንና ይህ ወጪ በማንና እንዴት እንደሚሸፈን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ፕሮጀክቱ የሚገነባውም “ላሙ”ተብሎ በሚጠራውና ለጦርነት ቀጣና ቅርብ በሆነው የሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የምዕራብ ኬንያ ክልል ውስጥ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል።

የላሙ ፕሮጀክት፤ የግዙፍ ወደብ ግንባታን፣  አገራቱን የሚያገናኝ የባቡር መስመርና የመንገድ ሥራን፣ የነዳጅ ማጣሪያ ጉድጓድ ቁፋሮንና ከደቡብ ሱዳን እስከ ኬንያ የሚደርስ የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ ቧንቧ መዘርጋትን እንደሚያጠቃልል  ተመልክቷል።

ፕሮጀክቱን አስመልክቶ  በላሙ በተዘጋጀው  ሥነ ስርዓት ላይ፤የኬንያው ፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪ፤ ከደቡብ ሱደኑ ሳልቫ ኪር እና ከኢትዮጵያው መለስ ዜናዊ ጋር   እጅ ለእጅ በመያያዝ   የፕሮጀክቱን መጀመር ይፋ በማድረግ የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ኪባኪ ባደረጉት ንግግር፦፡ ህዝቦቻችን እርስ በርስ ተገናኝተው በብዙ የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ  የጣልነው መሰረት እንደሚሳካና  ይህ ዕለትም በታሪክ የሚመዘገብ ታላቅ ቀን እንደሚሆን ጥርጣሬ የለኝም”ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ጠቅሷል።

አገራቱ ፡የሚገነቡትን “ላሙ” ወደብን ከኢትዮጵያና ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኘውን መንገድ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ለማጠናቀቅ ያቀዱ ሲሆን፤ ይህን ዕቅድ ያስቀመጡት ለመንገዱ  ማስጀመሪያ የሚሆን ገንዘብ በጋራ በማዋጣትና ሥራው ከተጀመረ በሁዋላ የውጪ ኢንቨስትመንትን በመሳብና በማፈላለግ በሚል ስሌት ነው።

የመንገድ ግንባታው ፕሮጀክት አስተዳደር  ስቴፈን ኢኩዋ  የፕሮጀክቱ እቅድ እጅግ ግዙፍ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።

“በአፍሪካ ከያዝናቸው ፕሮጀክቶች ይህ እጅግ ትልቁ  በመሆኑም ኩራት ይሰማኛል” ሲልም አክሏል።

የቢቢሲው ኖኤል  ምዋኩጉ ከዚያው ከላሙ ባስተላለፈው ሪፖርት ግን፤  ፕሮጀክቱ ከአፍሪካ እጅግ ውብ በሆነውና  ጥብቅ ክልል ሆኖ በቆየው  በላሙ የተፈጥሮና የ አካባቢ  ሀብት ላይ  በርካታ ተጽዕኖዎችን ሊያስከትል ይችላል የሚል ጭንቀት በ አካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ዘንድ መፈጠሩን  ጠቁሟል።

“ላሙ  በህይወት ያለና ሊኖር የሚገባ ታላቅ ቅርስ ነው። በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ማዕከል-(ዩኔስኮ) የተመዘገበ ታላቅ ቅርስ ነው። ይህ የተፈጥሮ ሀብት  በፕሮጀክቱ ምክንያት ታላቅ አደጋ አንዣቦበታል “ ያለው ደግሞ የሼቭ ላሙ( የላሙ አድን) ቡድን አባል የሆነው ሙአሊሙ ባዲ ነው።

ፕሮጀክቱን ለመስራት ወደ አካባቢው 500 ሺህ ሠራተኞች ከመጡ፤ በእርግጥም ቦታው የነበረውን ደረጃ ያጣል ሲልም ሚስተር  ባዲ ያክላል።

ከዚህም ባሻገር የ አካባቢው ነዋሪዎች በፕሮጀክቱ ምክንያት ቤት አልባ እንሆናለን በሚል ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ሚስተር ባዲ ገልጸዋል።

በነዋሪዎቹ  የተነሳውን የቤት አልባነት  ስጋት ለማስወገድ  መንግስታቸው ከወዲሁ  ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንት ኪባኪ ምላሽ ሰጥተዋል።

የአካባቢውን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች፤ በሶስቱ አገሮች ይፋ የሆነውን ይህን ታላቅ ፕሮጀክት፦ “አቅምንና አቋምን ያላገናዘበ ምኞት” በማለት ነው የጠሩት።

ተንታኞቹ  እቅዱ ሊሳካ እንደማይችል ከጠቀሷቸው ምክንያቶች አንዱ ፕሮጀክቱ ከአገሮቹ አቅም አካያ የተጋነነ መሆኑ ሲሆን፤ ሌላው ምክንያት ደግሞ እንዲገነባ የተመረጠበት ቦታና አካባቢ የጦርነት ቀጣና ከመሆኑ አኳያ ለአደጋ መጋለጡ አይቀርም የሚል ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ  በውስጥ አዋቂዎች በስፋት እየተወሳ ያለው ነገር፤ አዲሷ ነፃ አገር ደቡብ ሱዳን- በኢትዮጵያ ላይ ፈፅሞ እምነት ስለሌላት ፕሮጀክቱ አንድ ቦታ ላይ መቆሙ ወይም ችግር ማስከተሉ አይቀርም የሚለው ነው።

የደቡብ ሱዳን መንግስት ከሰሜን ሱዳን መንግስት የሚደርስበትን ተጽእኖ ለመቋቋም  በኬንያ እንዲሁም በኢትዮጵያ አልፎ ጂቡቲ የሚደርስ አዲስ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመዘርጋት መወሰኑ ይታወቃል።

ሰሜን ሱዳን አዲሱ ፕሮጀክት ህልውናዋን በቀጥታ የሚፈታተናት በመሆኑ ፣ የደቡብ ሱዳንን ውሳኔ በቀላሉ ላትመለከተው ትችላለች ተብሎአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide