አንድ የካናዳ ፓርላማ አባል በኢትዮጵያ ላይ ግፊት እንዲደርግ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ እንደሚጀመሩ አስታወቁ

ኢሳት (ህዳር 6 ፥ 2009)

የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊትን አጠናክሮ እንዲቀጥል አንድ ታዋቂ የሃገሪቱ የፓርላማ አባል ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻ በቅርቡ እንደሚጀምሩ  ለኢሳት ገለጹ።

አሌክስ ነታል የተባሉት እኚሁ የፓርላማ አባል ከተለያዩ አካላት ዘንድ የሚሰባሰበው የድጋፍ ፊርማ ለካናዳ መንግስት ቀርቦ የሃገሪቱ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ እንደሚያግዝ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የፓርማላ አባሉ በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት እየፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ሊነገረው ይገባል ሲሉ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላማዊ አገር ሆና ማየት እንፈልጋለን ያሉት የፓርላማ አባሉ ነታል፣ ሰላምና መረጋጋት ሰዎችን በመግደልና ስቃይን በመፈጸም ሊመጣ አይችልም ሲሉ ያደረባቸው ስጋት ገልጿል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የካናዳ የፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ ይፈጸማል ያሉትን ድርጊት በማውገዝ የሃገራቸው መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊትን እንዲያደርግ ዘመቻ መክፈታቸው ይታወሳል።

ከፓርላማ አባላቱ መቅረብ የጀመረውን ቅሬታ ተከትሎም የካናዳው ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ስቴፋኒ ዲዮን ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ምክክር ማካሄዳቸው የሚታወቅ ነው።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ሰኞ መግለጫን ያወጣው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ አስቸኳይ የፖለቲካ ስርዓት ማሻሻያ ተግባራዊ እንደሚደረግ አሳስቧል።

ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ የፓርላማ አባሉ አሌክስ ናታል ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻው የካናዳ መንግስት ግፊት እንዲወስድ እየቀረበለት ያለን ጫናን እንደሚያጠናክረው አከለው አስረድተዋል።

በካናዳ በተለያዩ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው ላሉ የህዝብ ተመራጮች በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማሳወቅ በመንግስታቸው የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያጋልጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።