አልሸባብ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ የምትገኘውን የታይገሎ ከተማን በቁጥጥሩ ስር አዋለ

ኅዳር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በበቆል ክልል በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አዋሳኝ ድንበር አዋሳኝ ላይ የምትገኘውን የታይገሎ ከተማን በከፍተኛ ውጊያ አስለቅቆ አልሸባብ ድጋሜ በቁጥጥሩ ስር ማዋሉን ሸበሌ ሚዲያ ዘግቧል። ከቅርብ ወራት ወዲህ ሃይሉን እያጠናከረ የመጣው አልሸባብ ቀድሞ በኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ስር የነበረችውን የታይገሎ ከተማን ለማስለቀቅ በመኪና ላይ በተጠመደ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት መታገዙን ሪፖርቶች አመላክተዋል።

ማክሰኞ እለት በከተማዋ ውስጥ በተደረገው ከፍተኛ ውጊያ አራት የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ወታደሮች መገደላቸውን እና ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ መማረካቸውን ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ገልጸዋል። በከተማዋ ዛሬም ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን በታይገሎ ከተማ በተደረገው ውጊያ ከሃያ በላይ ሰላማዊ ዜጎች  ሕይወታቸውን አጥተዋል። አልሸባብ ያደረሰውን ጉዳት  እንዲሁም የታይገሎ ከተማ በአልሸባብ ቁጥጥር ስር መዋሏን አስመልክቶ የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናት መግለጫ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። አልሸባብ የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ድንበር ከተማዋን ታይገሎን በቁጥጥሩ ስር ማዋሉ ተከትሎ በቀጠናው ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት  እየሆነ መምጣቱን ሸበሌ ሚዲያ አክሎ ዘግቧል።