የካቢኔ አባላት ሹመት ጸደቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 6/2011)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 16 የካቢኔ አባላትን ሹመት አጸደቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አቅራቢነት ሹመታቸው የጸደቀው ሚኒስትሮች ከኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶች የተውጣጡ ሲሆን ከተለመደው አሰራር ብዙም የተለወጠ ነገር እንዳልታየበትም አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

 

አራት ነባር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከነሚኒስትርነታቸው በቀጠሉበት በአዲሱ ካቢኔ አዲስ የሰላም ሚኒስቴር በሚል ለተቋቋመው ተቋምም ሚኒስትር ተመድቦለታል።

28 የነበሩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችን ወደ 20 በሰበሰበው አዲሱ አወቃቀር የሰላም ሚኒስቴር በሚል ለተሰየመው ተቋም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በሚኒስትርነት ተሹመዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ተነስተው ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ከአፋር ክልል ለስፍራው ተሹመዋል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በገንዘብ ሚኒስትርነት ሲሾሙ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ስፍራውን ለቀዋል።

የሕወሃት ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

የንግድ እንዲሁም የኢንደስትሪ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መላኩ አለበል እና ዶክተር አምባቸው መኮንን ካቢኔውን ለቀዋል።

የውጭ ጉዳይ፣ የውሃ፡መስኖና ኢነርጂ፣የትምህርት፣የጤና ጥበቃ እንዲሁም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ብቻ ባሉበት እንዲቀጥሉ የተወሰነ ሲሆን ሚኒስትሮቹም በሃላፊነታቸው እንዲቆዩ ተደርጓል።

አዲሱ ካቢኔ ከቀደመው አሰራር ብዙም የተለወጠ ነገር የለበትም በሚል ትችት እየቀረበበት ይገኛል።

ሹመቱ በኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹ ዙሪያ የታጠረ መሆኑም ታውቋል።