(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2011) የከተራ በዓል ዛሬ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከበረ።
ታቦታትም ከአድባራት ወተው በካህናት፣ በዲያቆናት እና በምዕመናን ታጅበው ወደየ ጥምቀተ ባህሩ ተወስደዋል፡፡
ታቦታት ወደ ማደሪያቸው ጥምቀተ ባህር ከደረሱ በኋላም አዳራቸውን በዚያው አድርገው በካህናትና ዲያቆናት ዝማሬና ሌሎች ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ተከናውነዋል።
የከተራ በአሉ በደመቀና በአሰደሳች ሁኔታ እንዲከበር ወጣቶች አካባቢዎቻቸውን በማጽዳት አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል።
በዓሉ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚከበር ቢሆንም የእስልምና እምነት ተከታዮችም ወንድማዊና እህታዊ አጋርነታቸውን ለመግለጽ በጽዳቱ መሳተፋቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።
ነገ በማግስቱ ደግሞ የጥምቀት በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በመላው ሃገሪቱ ይከበራል።
በዓሉ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መከበሩ እንዳለ ሆኖ በተለይም በጎንደር ከተማ የእምነቱ ተከታዮችን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት የመጡ ጎብኝዎች በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርዓት ይከበራል ተብሏል።
የከተራና የጥምቀት በዓላት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና የአደባባይ በዓላት መካከል ይጠቀሳሉ።