በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተቀሰቀሰ ግጭት 900 ያህል ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 9/2011) በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንኮ በምርጫ ዋዜማ በተቀሰቀሰ ግጭት 900 ያህል ሰዎች በሶስት ቀናት መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ ትላንት እንዳስታወቀው በሰሜን ምዕራብ ኮንጎ በሁለት ጎሳዎች መካከል በተፈጠረው ግጭትና በተከተለው እልቂት ሳቢያ በአካባቢው የሚደረገው ምርጫ እንዲራዘም ምክንያት ሆኗል።

ባኑና ባቲንዲ በተባሉ ጎሳዎች መካከል በ4 ቀበሌዎች ውስጥ በተከተለው ግጭት 900 ያህል ሰዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ ህንጻዎችና ቤቶች ወድመዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ በሰጡት መግለጫ 890 ሰዎች ተገድለው መቀበራቸውን አረጋገጠዋል።

ሌሎች ተገድለው አስከሬናቸው ኮንጎ ወንዝ ውስጥ የተጣሉና የተቃጠሉ መኖራቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶች እንዳሉም አመልክተዋል።

ላለፉት 20 አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ጆሴፍ ካቢላን ለመተካት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ህዳር 30/2018 በኮንጎ ምርጫ ሲካሄድ ዩምቢ በተባለውና እልቂቱ በተከሰተበት ግዛት ምርጫው እንዲራዘም ተደርጓል።

በግጭቱ 890 ሰዎች መገደላቸው ከመረጋገጡ ባሻገር 465 ቤቶችና ህንጻዎች ወድመዋል።–እንዲሁም ዘረፋ ተካሂዶባቸዋል።

ከወደሙት ሕንጻዎች ውስጥ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የጤና ጣቢያዎችና የምርጫ ኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ይገኝበታል።

በአብዛኛው ሰላማዊ እንደነበር በሚጠቀሰው በሰሜን ምዕራብ ኮንጎ ሪፐብሊክ ግዛት ችግሩ የተፈጠረው በሐገሪቱ ከነበረው የምርጫ ዝግጅት ጋር ተያይዞ በተከተለው ውጥረት እንደሆነም ከዘገባዎች መረዳት ተችሏል።

የምርጫው ውጥረት ባለበት ወቅት የባኑ ጎሳ አባላት የባህላዊ መሪያቸውን ቀብር በባቲንዲ ጎሳ አባላት መኖሪያ ለመቅበር በመንቀሳቀሳቸው ግጭቱ መፈጠሩ ተገልጿል።

የዛሬ ወር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከህዳር 16 እስከ 18 በሶስት ቀናት ብቻ ባኑና ባቲንዱ በተባሉት ጎሳዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት 890 ሰዎች አልቀዋል።

ግጭቱ በተከሰተባቸው 4 ቀበሌዎች አብዛኛው ነዋሪ የተፈናቀለ ሲሆን 16ሺ የሚሆኑት ድንበር ተሻግረው ጎረቤት ኮንጎ ብራዛቢል መግባታቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።