ሚያዚያ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ያለፉትን ሳምንታት በከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ ሆነው ያሳለፉት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ከማሺ ዞን የተፈናቀሉ አርሶአደሮች ወደ ቤታቸው ሲገቡ የተደበላለቀ ስሜት እንደፈጠረባቸው ለኢሳት ገልጸዋል።
“ንብረት ቢወድም ይተካል፣ በህይወት ተርፈን ወደ ቤታችን በመግባታችን እግዝአብሄርን እና የተባበሩንን ሁሉ እናመሰግናለን፣ ደስ ብሎናል” በማለት አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ ይፈለጉ ተፈናቃይ ተናግረዋል።
ሌላ ተፈናቃይም እንዲሁ ወደ ቤቱ ሲመለስ ደስታ እንደፈጠረበት ገልጾ፣ ሁኔታው አሁንም አስተማማኝ ባለመሆኑ ህዝቡ ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተለው ጠይቋል። በእናንተ እርዳታ እና ሀይል ወደ ቦታችን ለመመለስ መቻላችንን ተረድተናል ያለው ግለሰቡ ፣ የተወሰደባቸው ንብረት እንዲመለስም ጠይቋል
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአማራው ህዝብ ላይ የደረሰውን ግፍ እያወገዙ ነው።
እስከዳር ከአዲስ አበባ ባስተላለፈችው የስልክ መልዕክት ኢትዮጵያውያን ይህን የግፍ አገዛዝ በቃ ሊሉት፣ ሆ ብለውም ሊነሱ ይገባል ብላለች
አንድ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ ወጣትም እንዲሁ በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ የደረሰው መፈናቀል በጣም እንዳሳዘነው ገለጾ፣ ሆ ብለን በመውጣት ተቃውሞአችንን በማሰማት ከችግራችን መላቀቅ ይኖርብናል
በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመው ግፍ ኢትዮጵያውያን ባልሆኑ መሪዎች የሚፈጸም ነው የሚለው ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ህዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲነሳ ጥሪ አቅርቧል
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የሚኖር አንድ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ይህ ሁሉ ጉድ ሲሆን እኛ ዝም ብለን መቀመጣችን አልገባኝም፣ አንድ ነገር ማድረግ አለብን ብሎአል
አሁንም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ ከ2 ሺ በላይ አማርኛ ተናጋሪዎች በቻግኒ ከተማ እና አካባቢው ተበትነው ይገኛሉ። የመንግስት ባለስልጣናት እስካሁን ቀርበው እንዳላናገሩዋቸው በመግለጽ ላይ ናቸው።
በደቡብ ክልል በሚኒት ወረዳ ደግሞ ቁጥራቸው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አማርኛ ተናጋሪዎች ተፈናቅለው አሁንም ጫካ ውስጥ ይገኛሉ። ከተፈናቃዮች መካከል 7 ሰዎች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ከጉራፈርዳ ወረዳ የተፈናቀሉ ከ20 ሺ በላይ የአማራ ተወላጆች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም። መንግስት ተፈናቃዮቹን በክልላቸው ማስፈሩን ቢገልጽም የት አካባቢና መቼ እንዳሰፈራቸው እስካሁን ይፋ አላደረገም።