የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የሲቪክ ተቋማት መንግስት በዜጎቹ ላይ የሚፈጽመውን ወንጀል እያወገዙ ነው

ሚያዚያ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል ” የአማራ ህዝብ ስቃይ እንዲያበቃ ወያኔን መቅበር ይኖርብናል ” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ” ወያኔ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ያፈናቀላቸው አማሮች የመጀመሪያዎቹ የወያኔዎች የጥቃት ሰለባዎች አይደሉም። የመጨረሻዎቹም አይሆኑም። ወያኔ  ከነ ጸረ አማራ ፖሊሲው በስልጣን እስካለ ድረስና በአማራ ስም አማራውን እያፈኑ፣ እየሰለሉ ከወያኔ ፍርፋሪ እየለቀሙ ለመኖር የቆረጡ  ከአማራው መሃል የወጡ ከሃዲዎች አማራውን መቆጠጠር እስከቻሉ ድረስ የአማራ ህዝብ መራቆት፣ ስደት፣ ውርደት፣ ሰቆቃና ሞት የማይለዩት ህዝብ እንደሆነ  ይቀጥላል። ” ብሎአል።

 

ህዝባዊ ሀይሉ ” ወያኔ ይሉኝታ ያልዘራበት፣ ትእግስትን እንደፍራቻ፣ አርቆ  ሳቢነትን እንደሞኝነት የሚቆጥር በአማራው ላይ ቂምና  ጥላቻን ሰንቆ  የተነሳ ፣ ስለጀግንነቱና ስለወርቅ ዘርነቱ እጅግ የተሳሳተና የተጋነነ ግምት ያለው፣ ማንም ምንም አያደርገኝም በሚል ትምክህት ተወጥሮ የሚኖር ድርጅት በመሆኑን ከእንዲህ አይነቱ በራሱ ፕሮፓጋንዳና  ከንቱ ውዳሴ ከሰከረ ድርጅት ጋር የሚደረግ ትግል ያለምንም መወላወል በከፍተኛ እልህና ጭካኔ የሚካሄድ ብቻ ነው።” ብሎአል።

 

የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር በደቡብ አፍሪካ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በደቡብ አፍሪካ፣ ቤተ ኢትዮጵያ ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና ፣የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ማህበር በደቡብ አፍሪካ በጋራ ባወጡት መግለጫ ደግሞ ” ወያኔ/ኢህአዲግ በኦሮሞ፤በአማራ፤በሱማሌ፤በአኝዋክ ባጠቃላይ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በወያኔ ጥይት እየተገደሉ፣ እየተጨፈጨፉ፤በእስር ላይ የሚገኙ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚያደርሰውን  ወደር የለሽ የዘር ማተፋት ወንጀል፡ ግድያ፣ እንግልት እናወግዛለን ብለዋል።

 

ኢትዮጵያውያኑ ” ለሀገራችን አንድነት፣ ለሕዝባችን እኩልነት፤ ልእልና መከበር፤ የህግ የበላይነት እና የዲሞክራሲ መብቶች የሚከበሩባት የጋራ መኖሪያችን ለማድረግ በመተባበር ለመስራት መዘጋጀታችንን በማይታጠፍ ቃላችን ደግመን ደጋግመን እንገልጻለን” ብለዋል።

በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ስብስብ” በህዝብና በሀገር ላይ ቀልድ የለም” በሚል ርእስ ባወጡት መግለጫ ደግሞ ” ህዝባችን መስዋእትነት ከፍሎና ተንከባክቦ ባቆያትና እትብቱ በተቀበረባት ምድር የመኖር ነፃነቱን ከተነፈገ፣ ኢትዮጵያዊ

ማንነቱን በዘርና በቋንቋ እየተመነዘረ በገዛ ሀገሩ እንደ ባይታዋር ተቆጥሮ ከተባረረና ሜዳ ላይ ከተጣለ፡- ሀገር አለኝ ማለቱ ትርጉሙ ምንድን ነው?። ” ሲል ጠይቋል።

 

“የውጭ ባለሃብቶች ለም መሬታችንን ይዘው ኰርተውና ተንደላቅቀው ሲያርሱና ሲያለሙ በአንፃሩ የሀገሩን ባለቤት

የሆነውን ህዝብ የበይ ተመልካችና ተመፅዋች ሆኖ እየተንከራተተ የሚኖረው እስከ መቼ ይሆን?። ይህ ዓይነቱ አሳፋሪ እርምጃ እየተደጋገመ ከሄደስ የሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል? ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ ስርዓተ አልበኝነት ነግሶ ህዝቡ አቤት የሚልበት የፍትሕ ቦታ አጥቶ ሲተራመስ ስናይ ለመሆኑ በሀገሪቱ ላይ መንግስት አለ ወይ? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል።”ብሎአል መግለጫው።

 

ሰሞኑን በቤንሻንጉል አካባቢ በሽዎች በሚቆጠሩት የአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰው ከቤት ንብረታቸው የማፈናቀል አረመኒያዊ ድርጊት ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል መንግስት ቀርቶ በባዕዳን ወረራ ጊዜም ቢሆን ያልተፈፀመና በኢትዮጵያ የመንግስታት ታሪክም ታይቶ የማይታወቅ አስነዋሪ ተግባር መሆኑን የሚገልጹት የትግራይ ተወላጆች ስበስብ፣  ከዚህም አልፎ የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ደግሞ ድርጊቱን መፈፀሙ ብቻ ሳይሆን የህወሓት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናት  ወንጀሉን ለመሸፋፈን ሲሉ የሰጡትን መግለጫ በህዝቡ ህይወት ላይ  መቀለድና ማፌዝ መሆኑን በይፋ ማሳየቱ ነው ብለዋል።

 

መግለጫው በመጨረሻም ”  የህወሓት/ኢሕአዴግ መንግስት በወገኖቻችን ላይ እየፈፀመ ያለው አረሜናዊ ድርጊት ኢትዮጵያዊነት ስነ ምግባር ያልተከተለ፣ የህዝባችን ሕገ መንግስታዊና ዜግነታዊ መብት የሚጥስ፣ ዓለም አቀፋዊ የሰብኣዊ ፍጡር አያያዝ የሚፃረር የወንጀል ድርጊት በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም፣  በዚሁ የወንጀል ድርጊት ላይ የተሳተፉ ሰዎችም በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ፣ በትግራይ ህዝብ ስምና ደም ሲነግድ የኖረው ህወሓት  በተለመደው ባህሪው በወንድሞቻችን ላይ እየፈፀመ ያለው ጭካኔ የተሞላበት አረሜናዊ ድርጊት ሆን ተብሎ ወገን ከወገኑ ጋር ለማጋጨትና ጥርጣሬ ለመፍጠር የተደረገ በመሆኑ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ የጥፋት ፈንጅ መሆኑን በመገንዘብ የአንድነትና የሰላም ባላንጣ የሆነውን ድርጅት የሚፈፀመው ግፍ ከካድሬዎቹ በስተቀር ብዙሃኑን የማይወክል መሆኑን እንገልጻለን ብሎአል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጀርመናዊያን ከኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም የህወሀት/ ኢህአዴግን አገዛዝ ለፍርድ ለማቅርብ ፊርማቸውን እያኖሩ ነው።

ዘጋቢያችን ሀይሉ ማሞ ከሙኒክ ጀርመን እንደገለጸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በማጋለጥ አለማቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ  ጫና እንዲያሳርፍ ለማድረግ በተጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ ስርአት እስካሁን ከ1800 በላይ ጀርመናዊያን ፊርማቸውን አስቀምጠዋል።