የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት ዜና እረፍት በክልሉ ውስጥ የተለያዩ ስሜቶችን ፈጥሯል።

የካቲት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የ45 አመቱ ጎልማሳ አቶ አለማየሁ አቶምሳ በታይላንድ ባንኮክ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግላቸው ከቆየ በሁዋላ ትናንት አርፈዋል። የአቶ አለማየሁን እረፍት ተከትሎ የኦህዴድ አባላትና የክልሉ ነዋሪዎች ስለአሟሟታቸው ሚስጢር የተለያዩ መላምቶችን እያቀረቡ በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ያሰባሰብነው መረጃ ያመለክታል። አብዛኛው ህዝብ ግለሰቡ በተቃዋሚዎቻቸው ተመርዘው መሞታቸውን በማመን የአሟሟታቸው መንስኤ እንዲታወቅ ይፈልጋል።

የኦህዴድ አባላትም በጉዳዩ ላይ እየተወያዩ ሲሆን ችግሩ በአመራሩና በአባላቱ መካከል መከፋፈል እንዳይፈጥር አንዳንድ የድርጅቱ አባላት መግለጫ እንዲሰጥ ግፊት እያደረጉ ነው። የፕሬዚዳንቱ የግል ጠባቂ የሆነው ግለሰብ በተመሳሳይ በሽታ ላይ መገኘቱ ለጥርጣሬው በር እንደከፈተ ለማወቅ ተችሎአል።  አቶ አለማየሁ የኦህዴድ ሊቀመንበርነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ሳይለቁ እንደለቀቁ ተደርጎ የተለቀቀው ዜናም መነጋገሪያ መሆኑን ከድርጅቱ አባላት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አቶ አለማየሁ መሞታቸው እንደተሰማ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ለሚገኙ ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ፣ በከተማው የሚገኙ የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ሌሎች የኢህአዴግ ደጋፊ አባላት እንዲገኙና አስከሬን እንዲቀበሉ በማሰብ በከተማው ለሚገኙ ሁሉም የመንግስት መ/ቤቶች አስቸኳይ የስልክ መልዕክት ተላልፏል።

የአስክሬን አቀባበሉን ውጤታማና የተሳካ ለማድረግ ከመንግስት የስራ ሰዓት ውጭ ተሸከርካሪና ነዳጅን ጨምሮ ቀላል የማይባል የመንግስት ሃብት ይፈሳል በማለት የመስተዳደሩን ውሳኔ በመቃወም የመስተዳድሩ ሰራተኞች አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

ከአባታቸው አቶ አቶምሳ ሚጃ እና ከእናታቸው ወይዘሮ አየለች ብሩ በ1961 ዓ.ም ነው የተወለዱት አቶ አለማየሁ፣ የ3 ልጆች አባት ነበሩ።

የኦሮሚያ ምክር ቤት የአዲሱን ፕሬዚዳንት ሹመት ለማጽደቅ በሚቀጥለው ሳምንት ሊያደርገው የነበረውን ስብሰባ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙ ታውቋል። አቶ አለማየሁን እንዲተኩ አቶ ሙክታር ፣ አቶ አብዱላዚዝና ወ/ሮ አስቴር ማሞ በእጩነት መቅረባቸውን ለማወቅ ቢቻልም፣ ካፒታል የተሰኘው በአገር ቤት የሚታተም የእንግሊዝኛ ጋዜጣ፣ በሰበር ዜናው ወ/ሮ አስቴር ማሞ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ይፋ አድርጓል። ኢሳት የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም።