(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 20/2011)ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ያላት ልዮ ጥቅም ጉዳይ በታሪክና በህገ-መንግስቱ መሰረት በምክክርና ህግን በተከተለ ሁኔታ ብቻ እንደሚፈታ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።
የተለያዩ የአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮችን ሌላ መልክ በመስጠት አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳና እርስ በእርሱ እንዲጋጭ ለማድረግ እየተፈፀሙ ያሉ ሴራዎችን መላው ህዝብ እንዲታገል አቶ ለማ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት ጥሪውን ያቀረቡት በአዳማ ከተማ በተካሄደው 9ኛው የጨፌው ጉባኤ ላይ ከጨፌው አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።
አባላቱ በክልሉ ሰላም፣ የህግ የበላይነትን ማስከበር፣ ህገ-ወጥነትን በመከላከል፣ ክልሉ በአዲስ አበባ ላይ ካለው ጥቅም ጋር የተያያዘ እና ሌሎች በርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ በዚሁ ወቅት ህዝቡ ጠረፍ አካባቢ ይፈፀም የነበረውን የፖለቲካ ሴራ ወደመሃል አገር ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት ሊታገል ይገባል ብለዋል።
አቶ ለማ መገርሳ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል የሚወሰደውን ርምጃ እንደአብነት አንስተዋል።
የህዝቡን ጥቅም ማዕከል አድርጎ የሚሰራ አመራር እና ህዝቡ ሌሎች በሚቀርፁለት አጀንዳ መመራት እንደሌለበት አሰሳበዋል።
እንዲያም ሆኖ “ህገ-ወጥ ቤቶች ሲገነቡ ቁጭ ብሎ የሚመለከት አመራር እያለ ቤት እንዲፈርስ መደረጉ በራሱ ጥፋት ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
የቀበሌና የጎጥ አመራር እንዲሁም የከተሞቹ ካቢኔዎች ቤቶቹ ሲገነቡ ያለእነርሱ እውቅና መገንባታቸው፤ ከዚህም አልፎ ግንባታዎቹን በእጅ አዙር ህጋዊ ሲያስደርጉ በመቆየታቸው ግንባር ቀደም ተጠያቂ ናቸው ነው ያሉት።
ኦሮሞ እና ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላቸውን ጥቅም አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳሉትም ለውጡን ለመቀልበስ በዳር አገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች አሁን በአዲስ አበባ ጉዳይ አንዱን በሌላው በማስነሳት እርስ በእርስ ለማበላላት አየሞከሩ ይገኛሉ።እናም ህዝቡ ጉዳዩን በጥንቃቄ ማየት አለበት ብለዋል።
የአዲስ አበባ ጉዳይ በታሪክና በህገ-መንግስቱ መሰረት በምክክርና ህግን በተከተለ ሁኔታ ብቻ የሚፈታ እንደሚሆነም አቶ ለማ ገልጸዋል።