በወላይታ ሶዶ ቤቴ አይፈርስም ያሉ አዛውንት በግሬደር ተገጭተው ሞቱ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 20/2011)በወላይታ ሶዶ ቤቴ አይፈርስም ያሉ አዛውንት በግሬደር ተገጭተው መገደላቸውን ተከትሎ ግጭት ተቀሰቀሰ።

በከተማዋ በህገወጥ መንገድ ቤት ገንብታችኋል በሚል ከ2ሺ በላይ አባወራዎች  መፈናቀላቸው ተሰምቷል።

ከሳምንት በፊትም በዛው በወላይታ ኦቶና በሚባል አካባቢ ዘጠኝ መቶ የሚሆኑ ቤቶች መፍረሳቸውንና ነዋሪዎቹም አደባባይ ላይ እንዲወድቁ መደረጋቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

መነሻው ህገወጥ ግንባታ የሚል ነው ይላሉ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች።

ከሳምንት በፊት የመጀመሪያ ዙር ነው በሚል 900 የሚሆኑ ቤቶች ኦቶና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሃይል በቀላቀለ ርምጃ እንዲፈርሱ ተደረገ።ነዋሪዎቹም አደባባይ ላይ ተበተኑ ያላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት ባደረሱት መረጃ።

ትላንት የጀመረውና ሁለተኛ ዙር ነው የተባለው ህገወጥ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ ተካሂዷል ይላሉ።የአሁኑ ህገወጥ በሚል የተካሄደው ዘመቻ ግን የተለየና የህዝብን ቁጣ የቀሰቀሰ ነበር ይላሉ።

ለዚህ ምክንያት የሆነው ቤቶቹ ከመፍረሳቸውና ዜጎች ከመፈናቀላቸው ሌላ ቤቴ አይፈርስም ያሉ አዛውንት በግሬደር ተገጭተው መገደላቸው ነው ይላሉ።

ይሄ ደግሞ የነዋሪዎቹን ቁጣ ቀስቅሷል ብለዋል።

ህገወጥ በሚባለው የሚካሄደው ዘመቻ በሃይል የታገዘና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሆኑ የህዝቡ ስነልቦና ላይ ጫናን በሚፈጥር መልኩ መካሄዱ ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎታል ያላሉ የወላይታ ሶዶ ነዋሪዎች።

በዚህ ጫና ውስጥ እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አደባባይ ወድቀዋል።

በሶዶ ከተማ በአራቱም አቅጣጫዎች ነው በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል በሚል ቤቶች እየፈረሱና ዜጎች እየተፈናቀሉ ያሉት ይላሉ ነዋሪዎቹ።

በቀጣይም ይፈርሳሉ በተባሉ 12ሺ ቤቶች ላይ ምልክት ተደርጓል።እነዚህ ቤቶች ሲፈርሱ ደግሞ ሃይል በቀላቀለና የጸጥታ ሃይሎችን ጉልበት በጨመረ መልኩ መሆኑ የወላይታ ህዝብ ተበዳይነቱ እየበረታ እንዲሄድ አድርጎታል ባይ ናቸው።

የከተማዋ ነዋሪዎች እየተደረጉ ያሉትን ዜጎችን የማፈናቀል ዘመቻ ለመቃወም ሞክረዋል።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በወቅቱ ላቀረቡት ጥያቄ የተሰጣቸውም ምላሽ ህገወጥነትን አናበረታታም ወደፊትም የጀመርንውን የማፍረስ ዘመቻ አጠናክረን እንቀጥላለን የሚል ምላሽ ነው ።

ኢሳት የነዋሪዎቹን ቅሬታ ይዞ ምላሽ ለማግኘት ወደ ከተማዋና ዞን አስተዳደሮቹ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሊሳካለት አልቻለም።