የኦሮሚያ ቴሌቪዥን በኢቲቪ ምክንያት ከዓረብ ሳተላይት ተባረረ

መስከረም ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኦሮምኛ ቋንቋ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሰራጨት ውል ገብቶ ሥራ የጀመረው በኦሮሚያ ክልል መንግስት የሚተዳደረው የኦሮሚያ ቴሌቪዥን የኢትዮጽያ ቴሌቪዥንን(ኢቲቪ) ፕሮግራሞች በአማርኛ ቋንቋ ማስተላለፍ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ ከውል ውጪ ተንቀሳቅሰሃል በሚል ከዓረብ ሳት መባረሩ ተጠቆመ፡፡

ቀደም ብሎ ከዓረብ ሳት ጋር ውል የገቡ ጣቢያዎችን ጃም በማድረግ ወይም በማፈን ክስ ቀርቦበት ከዓረብ ሳት የተባረረው ኢቲቪ  ባለፈው ወር የአቶ መለስ ዜና ዕረፍት ከተነገረ በኃላ የዜና ክፍለጊዜ ፕሮግራሙን ወደ ኦሮሚያ ጣቢያ በማገናኘት ዜናዎችን ማቅረብ ጀምሮ ነበር፡፡

ይህን ሁኔታ የተረዱት የዓረብ ሳት ኃላፊዎች የኦሮሚያን ቲቪ ዓለም አቀፍ ሥርጭቱ እንዲቆም ወስነዋል፡፡በዚሁ መሰረት የአቶ መለስ መርዶ በተነገረበት ሰሞን የኦሮሚያ ዓለምአቀፍ ሥርጭት ሊቋረጥ ግድ ሆኗል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጣቢያው መደበኛ ሥርጭቱን በዓረብ ሳት እንዲቀጥል ለማግባባት ባለፈው አንድ ወር ሙከራ አድርገው ከተስፋ ባለፈ ውጤት ማግኘት እንዳልቻሉ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

አንድ ሰማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ምንጭ እንደተናገሩት ከዓረብ ሳት ውል ውጪ የፌዴራል መንግስት የቴሌቪዠን ሥርጭት አስተላልፉ መባላችን ትክክል አልነበረም፡፡በዚህም ምክንያት ጣቢያው መታገዱም ስህተት የለበትም ብለዋል፡፡በአሁኑ ወቅትም በጉዳዩ ላይ ከዓረብ ሳት ኃላፊዎች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ያለፈው ስህተት ታርሞ ጣቢያው በቅር ብ ጊዜ ወደአየር ተመልሶ ሊመጣ እንደሚችል ተስፋ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

አቶ በረከት ከዚህ ቀደም የኤርትራ ቴሌቪዥን ጣቢያን ለማፈን ሙከራ እንደማያደርጉ ከአረብ ሳት ባለስልጣናት ጋር የውል ስምምነት አድርገው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ የገቡትን ቃል በማፍረሳቸውና በኤርትራ ቴሌቪዥን ላይ የአፈና እርምጃ መውሰድ በመቀጠላቸው ኢቲቪ ከአረብሳት እንዲባረር መደረጉ ይታወሳል።

አቶ በረከት በአረብ ሳት ላይ የጀመሩትን የማታለል ዘመቻ በመቀጠል፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአማርኛ ዜናዎች በአረብ ሳት በሚተላለፈው በኦሮምኛ ፕሮግራም በኩል እንዲተላለፍ አዘው ነበር። ይህን ማጭበርበር የተረዱት የአረብ ሳት ባለስልጣናት የኦሮሞኛ ዝግጅቱ እንዲቋረጥ በማድረግ የአቶ በረከትን ስራ አጋልጣዋል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት በአረብ ሳት ሲያስተላለፍ የነበረው ዝግጀቱ በኢትዮጵያ መንግስት እንዲታፈን ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ፣ በአረብሳትና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የተጀመረው አለመግባባት እንደቀጠለ ነው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide