የእርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ እንዲያከሽፈው ተጠየቀ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 13/2010)በባሌ ጎባ በህወሃት መንግስት አማካኝነት የእርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ እንዲያከሽፈው ተጠየቀ።

የጎባ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የህዝቡን ተቃውሞ በማሳነስ ያደረጉት ንግግር ቁጣን ቀስቅሷል።

ምክትል አስተዳዳሪዋ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመንግስት ወታደሮች ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑም ታውቋል።

ይህን የህዝብ ቁጣ ለማስቀየስ በህዝቡ መሀል ሃይማኖትንና ብሄርን መነሻ ያደረገ ግጭት ለመቀስቀስ በመንግስት በኩል እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ካለፈው ሰኞ ህዳር 11 ጀምሮ የባሌ ጎባ ነዋሪዎች በስጋት ውስጥ ናቸው።

በተለይም በከተማዋ ነባር የሆኑና ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ነዋሪ ሆነው ለዘመናት የቆዩ ኢትዮጵያውያን በመንግስት በተቀነባበረ ጥቃት የተነሳ ያለፉትን ሁለት ቀናት በፍርሃትና ጭንቀት እንዳሳለፉት ለኢሳት ገልጸዋል።

የጥቃቱ መነሻ ደግሞ የጎባ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ወ/ሮ ትዘለኝ መሸቴ ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ከህዝብ የተሰበሰበውን እርዳታ ለመስጠት በዶሎመና በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ያደረጉት ንግግር መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ምክትል አስተዳዳሪዋ በንግግራቸው የኦሮሞ ወጣቶች ያቀጣጠሉትን ህዝባዊ ትግልና ተቃውሞ በማሳነስ የጸረ ሰላም ሃይሎች እጅ አለበት ማለታቸው በዝግጅቱ ላይ የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆችን ማስቆጣቱን የጠቀሱት ምንጮች ወዲያኑ ቁጣ መቀስቀሱንና ምክትል አስተዳዳሪዋ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መሞከሩን ገልጸዋል።

የመንግስት ታጣቂዎች ምክትል አስተዳዳሪዋን ለመከላከል በአጀብ መኪና ወደ ጎባ ከተማ የወሰዷቸው ሲሆን እስካሁንም በጥበቃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

ም/ል አስተዳዳሪዋ አርበኞች ግንቦት ሰባትንና ኦነግን በመጥቀስ በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደው ተቃውሞ የህዝብ አጀንዳ የለበትም፣ በጸረሰላም ሃይሎች የሚመራ ነው ማለታቸው ከፍተኛ ቁጣን ሲቀሰቅስ ንግግራቸውም መቀጠል ሳይችል መቋረጡን ነው ከምንጮች መረጃ ለማወቅ የተቻለው።

የህዝቡ ቁጣ እንዳይቀጣጠል የሚል ስጋት ያደረባቸው የመንግስት ባለስልጣናት አንድ ሴራ ማቀዳቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ለዚህም የጎባ ከተማ ነዋሪዎችን ከኦሮሞ ተወላጆች ጋር በማጋጨት የተቃውሞን አቅጣጫ ማሳት እንዲሆን በመፈለጉ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በከተማዋ ነዋሪ በሆኑ የሌሎች ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጸዋል።

ሱቆቻቸውን ማሸግ የአንዳንዶቹን ቤቶች ማፈራረስ የተጀመረ ሲሆን በተለይ በወላይታ ብሄር ተወላጆች ላይ የተለየ ጥቃት እንዲደርስባቸው ሆን ተብሎ መቀነባበሩን ለማወቅ ተችሏል።

የፖሊስና የጸጥታ ሃይሎች ባሉበት ጥቃት መፈጸሙን የሚገልጹት ነዋሪዎች ህዝቡ ይህንን ሴራ ባለማወቅ ግጭቱን እንዲባባስ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የህወሃት መንግስት የመጣበትን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቀየስ በሚል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በኢትዮጵያውያን መሀል የእርስ በርስ ግጭት እንደሚፈጥር በተደጋጋሚ የሚገለጽ ሲሆን ህዝብ ይህን አውቆ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በጨቋኙ ስርዓት ላይ የተባበረ ክንዱን እንዲያነሳ መልዕክት ማስተላለፉ አሁንም ቀጥሏል።