ሮበርት ሙጋቤ ስልጣናቸውን ለቀቁ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 12/2010)የዚምባቡዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀቁ።

ፕሬዝዳንቱ የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት የሀገራቸው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እሳቸውን ከመንበረ ስልጣናቸው ለማውረድ ባሉበት ሰአት መሆኑ ታውቋል።

በዚምባቡዌ ለ37 አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ ዛሬ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ከሮይተርስ ዘገባ መረዳት ተችሏል።

በዚምባቡዌ የሕግ አዉጪ ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱን በሕግ ለመጠየቅና ለመክሰስ እየተካሄደ ያለውን የፖርላማ ስርአት አቋርጠው አፈ ጉባኤው ጄኮብ ሙዴንዳ ሙጋቤ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ መላካቸውን ለምክር ቤቱ ይፋ አድርገዋል።

አፈ ጉባኤው የሙጋቤን የመልቀቂያ ደብዳቤ ሲያነቡ የምክር ቤቱ አባላት ደስታቸውን በጩሕት ሲገልጹ ዚምባቡዌያንም ወደ አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

ሙጋቤ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ በጻፉት ደብዳቤ ውሳኔውን በገዛ ፍቃዳቸው ያደረጉት እንደሆነና በሀገሪቱ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ለመፍቀድ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሀገሪቱ ምክር ቤት ሙጋቤን ሕገ መንግስታዊውን ስልጣን ለባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ለማስተላለፍ ሞክረዋል በሚል ነበር የ93 አመቱን አዛውንትና ለ37 አመት ሀገሪቱን የመሩትን ፕሬዝዳንት ዛሬ በሕግ ለመጠየቅ በመምከር ላይ የነበረው።

በዚህ መሃል ግን አፈ ጉባኤው ጄኮብ ሙዴንዳ ሂደቱን አቋርጠው ከሙጋቤ የተላከውን መልቀቂያ ለምክር ቤቱ አቀረቡ።–ጉባኤተኛውም በደስታና በጩህት ምላሽ ሰጥቷል።

የሙጋቤ ደብዳቤ እሳቸውን ማን እንደሚተካ ግልጽ ያደረገው ነገር ባይኖርም የሀገሪቱ ህገ መንግስት ግን ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንደሚረከቡ ደንግጓል።

የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፊሌኬሌዛ ፎኮ ሲሆኑ እሳቸውም የሙጋቤ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤ ደጋፊ ናቸው በሚል ይታማሉ።

ሌላኛው ምክትል ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ናንጋግዋ ናቸው።

የዚምባቡዌ ቀውስ የጀመረውም ከሳምንት በፊት ሙጋቤ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ኤመርሰን ናንጋግዋን ከስልጣን ማባረራቸውን ተከትሎ ነበር።

ሙጋቤ ምክትላቸውን ከስልጣን ማባረራቸው ባለቤታቸውን ለመተካት ነው በሚል ነበር የጦር አዛዦች ጣልቃ በመግባት ሙጋቤን በቁም እስር ላይ ያዋሏቸው።

ገዢው ፓርቲ ዛኑ ፒ ኤፍ ሰኞ ባደረገው ስብሰባ ሙጋቤን ከፓርቲው መሪነት አንስቶ ባለቤታቸውን ማባረሩ ይታወሳል።

ሮበት ሙጋቤም እስከ ሰኞ እኩለ ቀን ስልጣናቸውን እንዲለቁ ካለዛ ግን በሕግ እንደሚጠየቁ ፓርቲው ገልጾ ነበር።

ለተወሰኑ ቀናትም ቢሆን ሙጋቤ ካንገራገሩ በኋላ የሀገሪቱ ምክር ቤት ዛሬ እሳቸውን በህግ ለመክሰስ እየተወያየ ባለበት ሰአት የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለአፈ ጉባኤው መላካቸው ታውቋል።

ሙጋቤ ከስልጣን ያባረሯቸው የ71 አመቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ናንጋግዋ የግድያ ሙከራ ሊደረግብኝ ታቅዷል በሚል አሁንም ከሀገር ውጪ መሆናቸው ታውቋል።

ፓቲያቸው ዛኑ ፒ ኤፍ ርሳቸውን ለመተካት እንደሚፈልግም ሲዘገብ ቆይቷል።

“አዞው” በሚል የቅጽል ስም የሚጠሩት ናንጋግዋ እንደ ተንኮለኛ ፖለቲከኛ የሚታዩ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008 በተደረገው ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ላይ ለተሰነዘረው ጥቃት ተጠያቂ ናቸው በሚልም ስማቸው ይነሳል።

የሰው ደም በእጃቸው አለ በሚልም ተቀናቃኞቻቸው ያነሷቸዋል።

በ1980 ስልጣኑን የተቆጣጠሩት ሙጋቤ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ድህነት ዳርገዋል የሚል ወቀሳ ይሰነዘርባቸዋል።

እሳቸው ወደ ስልጣን ከወጡትበት ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ዚምባቡዌያን በ15 በመቶ ድህነታቸው እንደጨመረ ይገለጻል።