የኢኮኖሚ አሻጥር እየተፈጸመ ነው ሲሉ ዶ/ር አብይ አህመድ ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ/ም) ጠ/ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በ4ኛው ሃገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ጉባኤ ላይ ተገኝተው ነው። “ ከአዲሱ ጠ/ሚኒስትር መምጣት በሁዋላ የሚታዩ የኢኮኖሚ “ሳቦታጆች”፣ የሚፈጸሙ ቅጥፈቶች ህብረተሰቡ በንቃት ካልታገለው ትንሽ ተብሎ የሚናቅ እንዳልሆነ ግምት ሊሰጠው ይገባል።” ሲሉ ተናግረዋል። ዶ/ር አብይ ከእርሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት ጋር በተያያዘ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙትን አካላት በስም አልገለጹም። ይሁን እንጅ እርሳቸው ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ አካላት አሉ ማለታቸው የእርሳቸውን ወደ ስልጣን መምጣት ያልተቀበሉ ወገኖች እንዳሉና የኢኮኖሚ ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ እንደሆነ ከንግግራቸው ለመረዳት ተችሎአል።
ዶ/ር አብይ አዲሱ መንግስታቸው በባድመ እና በመንግስት የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ የወሰዳቸው የፖሊሲ ለውጦች ተራማጅ ናቸው ብለዋል። በባድሜ ጉዳይ ሞት አልባ ጦርነት እየተካሄ መሆኑን፣ የአገር ሃብት ለጦርነት እየዋለና ሰራዊቱ ሁሌ በስጋት በምሽግ እንዲቆይ መደረጉ ትክክል ባለመሆኑ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል። የኢህአዴግ ውሳኔ ኢትዮጵያውያንን በማህበራዊ ሚዲያው በማወዛገብ ላይ ነው። እርምጃውን ያደነቁ ሰዎች የመኖራቸውን ያክል፣ 70 ሺ ኢትዮጵያውያንን አጥተን እንደዋዛ ተሰጠ የሚሉ ሰዎችም ተቃውሞአቸውን እየገለጹ ነው። ኤርትራ ኢህአዴግ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ እስካሁን የሰጠቸው መልስ የለም።
በመንግስት የልማት ተቋማት ላይ የተላለፈው ውሳኔም እንዲሁ በኢትዮጵያውያን በኩል መከፋፈልን ፈጥሯል። አሁን ባለው ሁኔታ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቢሸጡ ፣ ድርጅቶችን የሚገዙት ገንዘብ ያላቸው የህወሃት የንግድ ተቋማት ይሆናሉ በማለት ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ ዶ/ር አብይ በበኩላቸው ሽያጩ ነጻና ግልጽ እንዲሆን ያገባናል የሚሉ አካሎች ሁሉ በቅርበት ሊከታተሉት ይገባል ሲሉ ስጋቱን ለመቀነስ ሞክረዋል።
የተቋማቱን መሸጥ አጥብቀው የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን ኢፈርትን የመሳሰሉ የኢህአዴግ ኩባንያዎች እንዲሸጡና ከገበያ እንዲወጡ ፣ እነዚህን ድርጅቶች በተመለከተም አዲሱ ጠ/ሚኒስትር እርምጃ እንዲወስዱ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ብሩ በመርህ ደረጃ ድርጅቶችን ወደ ግል ማዞር ትክክል ቢሆንም፣ ጊዜው ነው ወይ ሲሉ ጥያቄ ያቀርባሉ። ጠ/ሚኒስትሩ ከኢኮኖሚው በፊት ፖለቲካው ላይ ትኩረት ቢያደርጉ ይሻል ነበር ሲሉ ያስረዳሉ።