ሜቴክ ለኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ያቀረባቸው ቁሶች የማይሰሩ መሆናቸው ተጋለጠ

  (ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 30/2010)የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ  በቢሊዮን ብሮች  ወጪ ለኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ያቀረባቸው ትራንስፎርመሮች እና ሌሎች ቁሶች የማይሰሩ መሆናቸው ተጋለጠ።

የኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን በቢሊዮን ብር ያወጣባቸው እነዚህ ቁሶች የማይሰሩ በመሆናቸው ሜዳ ላይ ተጥለው አረም እየበቀለባቸው መሆኑን በምስል ተደግፎ ለኢሳት የደረሰው ዜና ያስረዳል።

የማይሰሩ  ቁሶች ሜዳ ላይ ተጥለው በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት ፣ ሜቴክ ተጨማሪ የማይሰሩ መሳሪያዎችን አሁንም በማቅረብ ላይ ይገኛል።

በሕወሃቱ የጦር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና በሌሎች የሕወሃት የጦር መኮንኖች ሲመራ የነበረው ሜቴክ ከፍተኛ የሃገር ሀብት ምዝበራ ከሚካሄድባቸው ተቋማት አንዱ የኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ነው።የኮርፖሬሽኑ ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ጥራት ያላቸውን መሳሪያዎች አወዳድሮ እንዳይገዛ በኮርፖሬሽኑ ውስጥ በግዢ ሒደት የሚሳተፉት የሕወሃት አባላት መሆናቸው በራሱ ችግር መሆኑም ተመልክቷል።

ቀደም ሲል የኮርፖሬሽኑ የግዢ ሃላፊ የነበሩትን አቶ ወንደሰን ረጋሳን በማንሳት የሕወሃት ሰዎች በግዢ ሒደቱ ላይ ዋና ተዋናይ እንዲሆኑ መደረጉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

አቶ ወንደሰን ረጋሳ ከሃላፊነት የተነሱት ጥራት የሌላቸው እቃዎች መግባት የለባቸውም በሚል ባቀረቡት ሙግት ነው።

በምትካቸው ወይዘሮ ደስታ ቢልልኝ የተባሉ የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አባል ተሹመዋል።

በኮርፖሬሽኑ የግዢ ክፍል ውስጥ ካሉት ገብረአማኑኤል ሃይለገብርኤል ጋር በመሆን ሁለቱ የሕወሃት አባላት ለሜቴክ የዘረፋ ርምጃዎቹ መንገድ መጥረጋቸው ተመልክቷል።

መስፍን ብርሃኔ የተባሉት ሌላው የሕወሃት አባል ዋና ተዋናይ መሆናቸው ተመልክቷል።

ሜቴክ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን 2 ሚሊየን ቆጣሪ ለማቅረብ 495 ሚሊየን 850 ሺህ ብር ከወሰደ በኋላ የቀረበው ናሙና ጥራት እንደሌለው ተገልጾ ውሉ ቢቋረጥም ለሜቴክ የተሰጠው ግማሽ ቢሊየን ብር አልተመለሰም።

በከፍተኛ ክፍያ በቢሊየን ብሮች ወጪ ከሜቴክ ለኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የቀረቡት ትራንስፎርመሮች የማይሰሩ በመሆናቸው ሜዳ ላይ ተጥለው አረም እየበቀለባቸው መሆኑ ተገልጿል።

አዲስ ክፍያ እየተፈጸመ ሌሎች የማይሰሩ ትራንስፎርመሮች በመግባት ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።

ሜቴክ የኤሌክትሪክ ገመድ በማቅረብ ላይ ቢሆንም ይህም ጥራቱን ያልጠበቀ ነው ይላል መረጃው።

ቢሊየን ብሮች ከፈሰሰበት በኋላ በአብዛኛው ከስራ ውጪ መሆኑም ተመልክቷል።

ከታቦር ሴራሚክስ የሚቀርበው ሲኒ/ኢንሱሌተም/ከፍተኛ ችግር እንዳለበት ከወጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።