(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት20 /2010)የኢትዮጵያ ፓርላማ በመጭው ሰኞ በሚያካሂደው ስብሰባ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሰይም ታወቀ።
በዚሁም መሰረት ኢህአዴግ የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ የሰየማቸው ዶክተር አብይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ይሾማሉ።
የዶክተር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት የፓርላማ ሹመት በመጭው ቅዳሜ ይካሄዳል ተብሎ የሕወሃት ንብረት በሆነው ፋና ሚዲያ ከተገለጸ በኋላ እንደገና ለሰኞ መቀየሩ ተገልጿል።
ፓርላማው በመጭው ሰኞ በሚያካሂደው ስብሰባ ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን ያስረክባሉ።
በዚሁ ርክክብም ዶክተር አብይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰየሙ በዚሁም ቃለ መሃላ ፈጽመው ስልጣኑን እንደሚረከቡ ነው የተነገረው።
ዶር አብይ አህመድ ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላም ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መቀመጫ በሌለው የኢትዮጵያ ፓርላማ የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጀት/ኦሕዴድን/ በመወከል የኢህአዴግ ሊቀመንበር የሆኑ ተመራጭ ናቸው።
በአጋር ድርጅቶች እና በቀሪዎቹ 3 የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የተሞላው የኢትዮጵያ ፓርላማ 547 መቀመጫዎች አሉት።
ከነዚሁ መካከልም 8 በተለያዩ ምክንያቶች ተጓድለው የማሟያ ምርጫ ያልተካሄደባቸው ናቸው።
ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በፓርላማ ከተሰየሙ በኋላ ካቢኒያቸውን የማዋቀር መብት አላቸው።
ምናልባት ግን የቀድሞው ካቢኔ እንዲቀጥል ከወሰኑ በዚሁም እንዲቀጥል ሊያደርጉ ይችላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በስልጣን ዘመናቸው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሁለት ጊዜ ካቢኔያቸውን ማዋቀራቸው ይታወሳል።
በአሁኑ ጊዜ ያለው ካቢኔ ፖለቲከኛ ባልሆኑ ባለሙያዎች የተሟላ እና ብዙዎቹ ከዩንቨርስቲ የተመለመሉ ዶክተሮችን ያካተተ ነው።