ሚያዚያ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢትዮጵያ በ2005 በጀት ዓመት ከኤክስፖርት ካገኘችው ገቢ ይበልጥ በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን በሐዋላ መልክ ያገኘችው ገቢ እንደሚበልጥ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተገኘ የጹሑፍ መረጃ አመልክቷል።
መረጃው እንደሚያሳየው በ2005 በጀት ዓመት አገሪቱ ከኤክስፖርት 3.1 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን ኢትዮጵያውያን ከውጭ ከሚልኩት ገንዘብ ደግሞ 3 ቢሊዮን 9 መቶ ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡ በ2004 በጀት ዓመትም ከሐዋላ እና ከኤክስፖርት ያገኘቸው ገቢ ተመሳሳይ ማለትም እያንዳንዳቸው 3.2 ቢሊየን ዶላር መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡
መረጃው የሐዋላ ገንዘብ በፍጥነት እያደገ ሲመጣ በአንጻሩ አገሪቱ እንደቡና ፣የቅባት እህሎችና ጥራጥሬና የመሣሠሉትን በመላክ የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ያሳያል፡፡
የኤክስፖርት ዘርፍ ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት ከያዘው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንጻር አፈጻጸሙ ደካማ መሆኑን መረጃው የሚጠቁም ሲሆን ከገቢ ንግድ ጋር ያለው የንግድ ሚዛን ጉድለት እየሰፋ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ያመለክታል፡፡በ2004 የገቢ ንግድ(ኢምፖርት) መጠን 11 ቢሊየን ዶላር ሲሆን በ2005 ዓ.ም ወደ 11. ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ብሎአል፡፡ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ ከሸቀጦች የገቢ ንግድ ወጪ ጋር ሲነጻጸር በሚጠበቀው ደረጃ ዕድገት ባላማሳየቱ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ በ2003 ዓ.ም ከነበረበት 5 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በ2005 ዓ.ም ወደ 8. ቢሊየን 400 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰፋ ማድረጉን መረጃው ጠቁሟል፡፡ ይህን የንግድ ሚዛን ጉድለት ለማጥበብ መፍትሔው ኤክስፖርትን ማሳደግ ነውም ብሏል፡፡
እጅግ የተለጠጠ ነው በሚል ትችት የሚቀርብበት የመንግስት የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ታሳቢ ከተደረገው ገንዘብ መካከል ብድርና እርዳታ አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ መረጃው እንደሚያሳየው ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ለጋሽ መንግስታት አገሪቱ ያገኘችው ዕርዳታ በ2005 ዓ.ም ማሽቆልቆል አሳይቷል፡፡
በ2004 በጀት ዓመት 1 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዕርዳታ የተገኘ ሲሆን በ2005 ዓ.ም ወደ 1.ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡ ይህም የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተገምቷል፡፡