ኢሳት ዜና:-ኮሚቴው ኖቬምበር 3፣ 2011 ለሱዳኑ ፕሬዚዳንት በላከው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፣ የመለስ መንግስት ከኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከራሱ የፓርላማ አባላትም
ሳይቀር በመደበቅ ለሱዳን የሰጠው ሰፊ የኢትዮጵያ መሬት ህጋዊ ተቀባይነት የለውም።
የድንበር ኮሚቴው የመለስ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ ከመሬቱ አልተፈናቀለም እያለ ቢናገርም፣ ሚስጢራዊ ሰነዶችን በማውጣት ታወቀው ዊኪሊኪስ የመለስ መንግስት ሰፊ የሆነ ለም መሬት ለሱዳን መስጠቱን ከበቂ በላይ ማረጋገጡን ጠቅሶአል።
የሱዳኑ መሪ የአፍሪካ ህብረት በ1960ዎቹ ካይሮ ላይ ተገናኝቶ የወሰነውን ውሳኔ እንዲያከብሩ እና ያለ ኢትዮጵያ ህዝብ እውቅና በስውር የተደረሰውን ስምምነት እንዲሰርዙ አበክሮ አሳስቦአል።
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ሆነ ለወደፊቱ ህዝባዊ ተቀባይነትና ድጋፍ በሌለው በመለስ መንግስት ለሱዳን የተሰጠው ሰፊ መሬት ትክክል ነው ብሎ ስለማያምን፣ መሬቱን ለማስመለስ ማንኛውንም አይነት እርምጃ እንደሚወስድ ኮሚቴው አስታውሷል።
ዊኪሊኪስ የኢትዮጵያ መንግስት 1 ሺ ኪሎሜትር ርዝመት በ30 ኪሎሜትር ስፋት ያለው ሰፊ መሬት ለሱዳን አሳልፎ መስጠቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ በአማካሪነት ተቀጥረው የሚሰሩት እንግሊዛዊው ዲፕሎማት ፓትሪክ ጊልከስ ለአሜሪካ ባለስልጣናት እንደገለጡት የመለስ መንግስት እጅግ ከፍተኛ የሆነ መሬት ለሱዳን መስጠቱን ገልጠዋል።
የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ፓርላማው ያላጸደቀው ስምምነት አሳሪነት የሚኖረው ባለመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ታማኝ መሪ በምታገኝበት ጊዜ መሬቱዋን መልሳ የማግኘት ሰፊ እድል ይኖራታል ይላሉ።
የአፍሪካ ህብረት በ1964በየካይሮ ባደረገው ስምምነት የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ጊዜ በያዙት ድንበር ይጸናሉ በማለት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።
አቶ መለስ ይህን ስምምነት በመጣስ በግላቸው ሰፊ የሆነውን የኢትዮጵያን ግዛት ለሱዳን መስጠታቸው አለማቀፉን ህግ መጻረራቸውን እንደሚያሳይ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የመለስ መንግስት ግን ለሱዳን የተሰጠ መሬት የለም በማለት ለማስተባበል ይሞክራል።
ለፖለቲካ ስልጣኑ በማሰብ የአገሩን መሬት እንደ አምባሻ እየቆረሰ ለሌላ አገር የሚሰጥ መሪ በታሪክ ታይቶም ተስምቶም አይታወቅም በማለት በምርጫ 2002 የተቃዋሚ መሪዎች መንግስትን ሲተቹ እንደነበር ይታወሳል።