አርቲስትና የመብት ተሟጋች ደበበ እሸቱ አርብ እለት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ብቻውን በዝግ ችሎት ቀረበ

ዳኛ ታሪኳ ተበጀ  በሚያስችሉት  አንደኛ  ወንጀል  ዝግ  ችሎት  ላይ  ማንኛውም  የተከሳሽ ቤተሰብ፣ ጋዜጠኛ፣ የመብት ተሟጋችና ታዛቢዎች እንዲገቡ አልተፈቀደም፡፡

ከተከሳሾቹ  ቀደም  ብለው  ፍርድ  ቤቱን የከበቡት  ፌዴራል  ፖሊሶች  በችሎቱ  አቅራቢያ ማንኛውም  ሰው  እንዳይጠጋ  የከለከሉ  ሲሆን ሦስት ጋዜጠኛች ብቻ የፖሊሶችን ከለላ በትግል አልፈው  የፍርድ ቤቱ  መዝገብ  አመላላሽ  ጋር በመድረስ “እኛ ጋዜጠኞች  ነን ፖሊሶች ከልክለውን ነው፣ እባክሽን ዳኟዋ ጋር ሂጂና እንድንገባ እንድትፈቅድልን ጠይቂልን”  በማለት መታወቂያቸውን ያሳይዋት ሲሆን ፣ ወደ
ችሎቱ ገብታ ስትመለስ አዝናለሁ መግባት አትችሉም  ብላችኋለች ማለቱዋን ዘጋቢአችን ገልጧል፡፡

ከችሎቱ በኋላ ሪፖርተራችን ያናገራቸው  የተከሳሽ ተከላካይ ጠበቃ ሞላ ዘገየ ስለችሎቱ እንደገለጹት መጀመሪያ ዳኛዋ ችሎቱን ስታስጀምር እስከ ዛሬ ደንበኛዬ በማዕከላዊ እሥር ቤት በቆየበት ጊዜያት ሁሉ ፖሊስ ባለመፍቀዱ አግኝቼው  እንደማላውቅ  ገልጬላት ቃል ከመስጠቱ በፊት መመካከር እንደምፈልግ ጠይቄያት ለ5 ደቂቃ ያህል ላነጋግረው  ችያለሁ ብለዋል፡፡

በሁኔታው  ግራ የተጋባች  የምትመስለው  ዳኛ ታሪኳ ተበጀ ተከሳሾች በጠበቃ  የመጎብኘት፣ የመመካከር እና የመጠየቅ ሕገ- መንግሥታዊ መብታቸው  እንጂ ማንም  የሚሰጠውና የሚከለክለው አይደለም፤ ይህን ሂደህ አሁኑኑ ለአለቃህ ንገረው ስትል መርማሪውን አዛለች ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ  ዐቃቤ- ሕግ “የማሰባስበው መረጃ አለኝ፣ ምርመራዬንም  አልጨረስኩም ብሎ ተጨማሪ የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ፣ ጠበቃው በበኩሉ ” “ፖሊስ መረጃና ማስረጃ አለኝ ብሎ ከአሰረ በኋላ እንደገና መረጃና ማስረጃ ለማፈላለግ በየጊዜው ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ የሚጠይቅበት ሁኔታ አግባብ አይደለም” የሚል መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል። ይሁን እንጅ ዳኛዋ የዐቃቤ- ሕግን ጥያቄ
ተቀብለው  ለህዳር 22 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ ዜና ከሁለቱ ስዊድናዊያን ጋራ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በዋና ወንጀል አድራጊነት የተከሰሱት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) አባላት የኾኑት አብዲወሊ መሐመድ እስማኤል እና ከሊፍ ዐሊ ዳሂር የ17 ዓመት ጽኑ እሥራት  ተፈርዶባቸዋል።

በእነ እስክንድ ነጋ፣ ውብሸት ታዬ ፣ ዘመኑ ሞላና ሌሎችም እስረኞች ላይ መንግስት ከአሰረ በሁዋላ መረጃ እያፈላለገ መሆኑን የህግ ባለሙያዎች እየተቹት ነው። አቶ መለስ ዜና በቅርቡ በፓርላማ ተገኝተው በተከሳሾች ላይ በቂ ማስረጃ አሰባስበናል ማለታቸው ይታወሳል።  የመለስ መንግስት ተቺ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን በሽብርተኝነት ስም እያሰረ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ምንም እንኳ እስካሁን በኢትዮጵያ የአረቡ አለም አይነት አብዮት ባይነሳም፣ ብዙዎች ግን ምልክቶች በእየአቅጣጫው እየታዩ ነው በማለት ጋዜጦች በመጻፍ ላይ ናቸው። ፍትህ ጋዜጣ አርብ እለት ባወጣው እትም  የመለስ መንገስት ከጋዳፊ አወዳደቅ ተምሮ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ መክሯል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ውድነቱ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱ እንዲህ አይነት አስተያየቶች እንዲቀርቡ እያደረገ ነው።