በአውሮፓ የሚኖሩ ሙስሊሞች መንግስት አህባሽ የተባለውን የእስልምና አስተምህሮ ለማስፋፋት እቅድ ዘርግቶ መንቀሳቀሱን አወገዙ

ኢሳት ዜና:-1 ሺ 4 መቶ 33ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል  በብራሰልስ፣  ቤልጂም በተከበረበት ወቅት የሉቅማን ኢትዮጵያዊያን ቤልጄማውያን ሙስሊሞች ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት  አብዩ ያሲን  መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ቀርጾ  አህባሽ የተባለውን የእስልምና አስተምህሮ ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን  የጽሁፍና የንግግር ማስረጃዎችን በማቅረብ ለተሳታፊው አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በአለማያ ከተሰጠው ስልጠና በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ መንግስት በሰንዳፋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ውስጥ 200 የሚሆኑ የአህባሽ አሰልጣኞችን እያሰለጠ መሆኑን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ እነዚህም ሰልጣኞች እስከ 30 ሺ የሚጠጉ ሙስሊሞችን ያሰለጥናሉ ተብሎ እቅድ መዘርጋቱን ተናግረዋል።

አህባሽ የተባለው አስተምህሮ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰለም አስጊ መሆኑን የተናገሩት አቶ አብዩ ያሲን፣ መንግስት የአገር አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥል፣ የእርስ በርስ ግጭቶችን ሊፈጥር የሚችል እምነት ለመደገፍ ለምን እንደተነሳሳ ግራ እንደገባቸው አልሸሸጉም።

አቶ አብዩ በማብራሪያቸው መንግስት በህገመንግስቱ የሰፈሩትን መብቶች መርገጡን ጠቅሰው፣ አሁን የሚታየው አንዱን አስተምህሮ ደግፎ ሌላውን የማውገዝ አካሄድ የአገርን ሉአላዊነት የሚጎዳ ፣ ህዝቦች ለዘመናት ተቻችለው የኖሩበትን ስርአት የሚያጠፋ፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ያላቸውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት፣ የሙስሊሞችን እና የእስልምናን መልካም ምስል
የሚያበላሽ በአጠቃለይ በአጼው ዘመን ወደ ነበረው ታሪክ መልሶ የሚወስድ መሆኑን ተናግረዋል:: ሊቀመንበሩ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዬውን አደገኛ ሁኔታ መቀየር የሚቻልባቸውን መንገዶችም ዘርዝረዋል::

በበአሉ ላይ ከተገኙት ሙስሊሞች መካከል አቶ ገአስ አህመድ የተባሉት የቤልጂየም ነዋሪ፣ የአህባሽ መሪዎች አስተምህሮውን በአገር ውስጥ እንደማንኛውም የእምነት ተቋም ለማስፋፋት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የመብት ጉዳይ በመሆኑ እንደማይቃወሙት ገልጠው፣    ይሁን እንጅ መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ቀርጾ ፣ በጀት መድቦና ሰዎችን አሰልጥኖ እምነቱን ለማስፋፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች ሙስሊሞች እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።

በብራሰልስ በተከበረው በአል ላይ  አስገራሚ ትእይንትም ታይቷል። ብራሰልስ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ የተወከሉት የህዝብ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ሀላፊ አቶ ተፈሪ መለሰ፣ የኮንሱላር ጉዳዮች ሀላፊ አቶ ገብሩ ግደይ፣ እና የዲያስፖራ ጉዳዮች ሀላፊ አቶ መስፍን ውድነህ በበአሉ ላይ  ይገኛሉ። የበአሉን መጀመር ቁጭ ብለው እየተጠባበቁ በነበረት ጊዜ የግንቦት7 ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበበ ቦጋለ በስፍራው ይገኛሉ።

በዚህን ጊዜ የኢምባሲው ልኡካን አባለት የግንቦት7 ተወካይ ባሉበት አብረን አንሰበሰብም በማለት አዳራሹን ለቀው ወጡ። የሙስሊሞቹ ተወካይም ባለስልጣኖቹ እንዲመለሱ ለማግባባት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም
ተወካዮቹ ግን በፓርላማ አሸባሪ ከተባለ ድርጅት መሪ ጋር አብረን ብንታይ ፣ ድርጅቱን መደገፍ መስሎ ስለሚቆጠርብን ለመሳተፍ ፈቃደኞች አይደለንም በማለት በአሉን ሳይካፈሉ ወደ መጡበት ተመልሰዋል። የኢምባሲው ተወካዮች ድርጊት ያሳዘናቸው ሙስሊሞችም፣ “የኢምባሲው ሰራተኞች የኢትዮጵያ ኢምባሲ ተወካዮች ናቸው ወይስ የኢህአዴግ ኢምባሲ ተወካዮች ናቸው?”ሲሉ ጠይቀዋል።

በበአሉ ላይ የተለያዩ ሙስሊሞችም የደስታ መልእክቶችን አስተላልፈዋል፤ በአቶ አብዩ ያሲን የቀረበውን ጥናታዊ ትንተና  በሚቀጥለው ሀሙስ ይዘን የምንቀርብ በመሆኑ ውድ ተመልካቾቻችን እንዳያመልጣችሁ በአክብሮት እንጋብዛለን።