የኢትዮጵያ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት እጅግ ማሽቆልቆሉን አንድ ጥናት አመለከተ

ኢሳት (ጥር 18 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላለፉት ተከታታይ አስር አመታት ማሽቆልቆል ማሳየቱን በ167 የአለማችን ሃገራት ላይ ጥናቱን ያካሄደ አንድ የአለም አቀፍ ተቋም ይፋ አደረገ።

ይኸው የዘ-ኢኮኖሚስት አለም አቀፍ መጽሄት እህት ኩባንያ የሆነውና በደህንነት ዙሪያ ጥናትን የሚያካሄደው ኢኮኖሚስት አንተሊጀንስ ዩኒት ኢትዮጵያ ከ10 አመት በፊት አስመዝግባ የነበረው የ4.7 ነጥብ ባለፈው የፈረንጆች አመት ወደ 3.6 ነጥብ ማሽቆልቆሉን ገልጿል።

አመታዊ ሪፖርቱን ለህዝብ ይፋ ያደረገው ድርጅቱ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሂደት መሻሻል ባለማሳየቱ ምክንያት ሃገሪቱ ጨቋኝ ተብለው ከተቀመጡ የአለማችን አገራት ተርታ ልትመደብ መቻሏን በሪፖርቱ አስፍሯል።

የደህንነት ተቋሙ የተለያዩ መስፈርቶችን በመውሰድ ለሃገራት ከ10 በሚሰጠው ነጥብ ኢትዮጵያ እንደፈረንጆቹ አቆጣጣር በ2007 አም 4.7 በማስመዝገብ የመጨረሻ የተሻለ ውጤትን አስመዝግቦ እንደነበር አውስቷል።

ይሁንና የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሁኔታ መሻሻል ከማሳየት ይልቅ ባለፉት 10 ተከታታይ አመታት ማሽቆልቆልን በማሳየት በተለይ ከ2010 አም ጀምሮ የከፋ እየሆነ መምጣቱን አመልክቷል።

የሃገሪቱ ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸው ዕምነትን በዋና መስፈርት የወሰደው ድርጅት የዴሞክራሲ ግንባታዎችን ጨምሮ 60 አበይት ጉዳዮች በጥናቱ ለግብአትነት መዳሰሳቸውን አክሎ ገልጿል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጣር ከ2005 አም የተካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎ በኢትዮጵያ ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸው እምነት እየቀነሰ ከመምጣቱ ጎን ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ የሚያደርጉት ጥረት አፈና እየተጠናከረበት መምጣቱ ተመልክቷል።

የአለም ሃገራት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሃገሪቱ ላይ የሚያወጧቸው የሰብዓዊ መብት መረጃዎችና የሚገልጿቸው ስጋቶች በዚሁ አለም አቀፍ ጠቋሚ ሪፖርት ውስጥ መካተታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2005 አም የተካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎ በኢትዮጵያ ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸው እምነት እየቀነሰ ከመምጣቱ ጎን ሰዎች ሃሳባቸው በነጻነት ለመግለጽ የሚያደርጉት ጥረት አፈና እየተጠናከረበት መምጣቱ ተመልክቷል።

የአለም ሃገራት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሃገሪቱ ላይ የሚያወጧቸው የሰብዓዊ መብት መረጃዎችና የሚገልጿቸው ስጋቶች በዚሁ አለም አቀፍ ጠቋሚ ሪፖርቱ ውስጥ መካተታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

በአለማችን የዴሞክራሲ ተምሳሌት ተደርጋ የምትነሳው አሜሪካ በ2015 አም አስመዝግባ የነበረው 8.05 ነጥብ በ 2016 አም ወደ 7.9 መጠነኛ መቀነስን በማሳየት አሁንም ድረስ በግንባር ቀደምትነት ተቀምጣለች።

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ለስልጣን እንዲበቁ ያደረጓቸው ሁኔታዎች ሃገሪቱ የዴሞክራሲ ሁኔታዋ መጠነኛ ለውጥ ሊያሳይ መቻሉን ኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ዩኒት በሪፖርቱ አመልክቷል።

ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ጃፓን በሪፖርቱ የተሻለ ነጥብን በመያዝ በዋናነት የተቀመጡ ሲሆን፣ ብሪታኒያ ከ38 የአለማችን ሃገራት ጋር የዴሞክራሲ ስርዓቷ ላይ ማሻሻያ ማስመዝገቧም ታውቋል።

ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ ከ10 ነጥብ 7.4 ነጥብን በመያዝ ግንባር ቀደም ሃገር ተደርጋ ተቀምጣለች። አብዛኞቹ የአህጉሪቱ ሃገራት መሻሻልን ከማሳየት ይልቅ የዴሞክራሲ ግንባታቸው እያሽቆለቆለ መሆኑንም ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።