ሰኔ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እየተገባደደ ባለው የኢትዮጵያዊያን የ2005 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ማለትም ከሐምሌ 1/ 2004 እስከ መጋቢት 30/ 2005 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ዋናዎቹ የወጪ ንግድ ምርቶች በዓለም ገበያ ገቢያቸው ማሽቆልቆሉን ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተገኘ መረጃ ጠቁሟል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜያት 2 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህ ገንዘብ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር
ሲነጻጸር በ5 በመቶ የጨመረ ቢሆንም ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸሙ አነስተኛ መሆኑ ታውቋል፡፡
በነዚህ ወራት በተለይም የኢኮኖሚ ዋልታ የሚባለው ቡና ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ገቢው ቀንሶ ታይቷል፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከቡና 528 ሚሊየን ዶላር ሲገኝ ዘንድሮ ግን ወደ514 ሚሊየን ዝቅ ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የቁም ከብት፣ ስጋና የስጋ ውጤቶች ከ219 ሚሊየን ዶላር ወደ 188 ሚሊየን ዶላር ፣
ቅመማቅመም ከ29 ሚሊየን ዶላር ወደ 21 ሚሊየን ዶላር፣ አበባ ከ138ሚሊየን ዶላር ወደ 135 ሚሊየን ዶላር አሽቆልቁለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ እስከ መጋቢት ወር ድረስ ወደ ውጪ ከተላኩት ምርቶች ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ጭማሪ ካሳዩት ምርቶች መካከል የቆዳ ውጤቶች፣ ጥራጥሬ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ወርቅና የቅባት እህሎችና ጫት ይገኙበታል፡፡ የጫት 199 ሚሊየን ዶላር የዘጠኝ ወራት ገቢ ከቁምከብት፣ሥጋና የስጋ ውጤቶች፣ከቅመማቅመም እንዲሁም ከአበባ ከተገኘው ጋር ሲነጻጸር የላቀ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡
በዓለም ገበያ ፍላጎት ያላቸውን የወጪ ምርቶች መጠን መጨመርና ገቢን ማሳደግ አግባብ ቢሆንም የዋናዋና ምርቶች ገቢ ማሸቆልቆል አሳሳቢ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡