ጥቅምት ፲፪(አስራ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መድረክ በስዊድን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኒታን በተመለከተ በተለይም በቅርቡ በስዊድን ቴሌቪዥን የኦጋዴን ህዝብ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ያሳየውን ዶክመንትሪ ፊልም የተመለከቱ የስዊዲን የህግ ጠበቃና የአለም አቀፍ የህግ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጁሪስት ስቴላ ያርዴት የመንግስት ባለስልጣናትን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለመክሰስ እንደተዘጋጁ በማስታወቃቸው እሳቸውንና ሌሎችን እንግዶች በመጋበዝ ኖቬምበር 2 ቀን 2013 ዓ.ም የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
በጉራፈርዳ፤በቤንሻንጉል፤በአሶሳ፤በአርባጉጉና በወልቃይት በአፋር በኦሮሞና በአማራው ህዝብ ላይ ጭምር የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች፣ ከአራት መቶ ህዝብ በላይ የአኝዋክና የጋምቤላ ህዝብ በጅምላ መጨፍጨፋቸውን የሚያወሱ ገለጻዎች ይደረጋሉ።
በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ እኝሁ ስዊዲናዊው የህግ ኮሚሽነር ስለተነሱበት ክስ መግለጫ የሚሰጡ ሲሆን ዶክቶር ሙሉዓለም አዳም ከኖርዌ በመምጣት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ገጽታና አሁን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ንግግር ያደርጋሉ።
በኢትዮጵያ እስር ቤት ለአመታት ታስረው የቆዩት ስዊዲናዊው ጋዜጠኛ ማርቲን ሸቤ ስለእስራቱ ሁኔታ ተጨማሪ ገለጻ የሚያደርጉ ሲሆን ይሄንንኑ የእስር ሁኔታ የሚገልጸውን በቅርቡ ያሳተሙትን መጽሃፍ ይዘው እንደሚቀርቡ ታውቋል።
በስዊዲን ቴሌቪዥን ቀርቦ በአሁኑ ሰዓት የአለም መነጋገሪያ የሆነውን ፊልም ቀርጸው በድብቅ ይዘው በመውጣት ለዓለም ህዝብ ይፋ ያደረጉት የውጋዴን ክልል ፕሪዝዳት የቅርብ ሰው የነበሩት አብዱላሂ ሁሴንም እንዴት ፊልሙን ሊቀርጹ እንደቻሉ፤ ይዘው ለመውጣት ያሰቡበት ምክንያትስ ምን እንደሆነ፤ እንዲሁም ፊልሙን ይዘው ሲወጡ ስለገጠማቸው ችግሮች በቦታው ላይ በመገኘት ለተሰብሳቢው ገለጻ ያደርጋሉ።
መቶ አለቃ አበረ አዳሙ በኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ስር በተለያዩ የሃላፊነት ቦታወች የሰሩና የኢ.ፒ.ፒ.ኤፍ መስራችና የአመራር አባል የነበሩ ደግሞ በኢ ትዮጵያ ውስጥ በስራ ላይ በነበሩ ግዜ ይሰሩ ስለነበረው ሁኔታ የሚያውቁትን በመናገር የኢትዮጵያን መንግስት ስውር ገበና እንደሚያጋልጡም ይጠበቃል።
የኢሳት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ወንድማገኝ ጋሹም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ በቪዲዮና በልዩ ልዩ መረጃዎች የተደገፈ ማብራሪያ እንደሚያቀርብ ታውቋል።
በዚህ ውይይት ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተካፋይ እንዲሆን ጥሪ የተደረገ ሲሆን ስዊዲናዊው የህግ ኮሚሽነር ለሚያቀርቡት ክስ ይረዳል የሚል መረጃ ያለው ግለሰብም ካለ በቦታው ተገኝቶ በተጨባጭ ሁኔታ መረጃውን ይዞ ማቅረብ እንዲችል ጥሪ ቀርቧል።
በዚህ የውጪ ሀገር ሰዎች በሃገራችን ጉዳይ በሚካፈሉበት ታሪካዊ የውይይት መድረክ ላይ ብዙ ህዝብ ተሳታፊ እንደሚሆን የገለጹት የውይይቱ አዘጋጆች፣ ውይይቱ ስቶኮልም ውስጥ በሃሉንዳ ፎልክት ሂዩስ ከ 13፤00 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።