ኦብነግ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

ጥቅምት (አስር)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት በም/ጠ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሚመራው የልኡካን ቡድን ላይ ጥቃት ፈጽሞ በርካታ ወታደሮችን መግደሉን የግንባሩ ቃል አቀባይ ለኢሳት ገለጹ።

አቶ ሀሰን አብዱላሂ እንደገለጹት ጥቃቱ የተፈጸመው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ9 የክልል መሪዎችንና ባለሀብቶችን አስከትለው በአካባቢው ጉብኝት ለማድረግ ቀብሪደሀር አየር ማረፊያ ባረፉበት ወቅት ነው።

ባለስልጣኖቹ ጉበኝት እንደሚያደርጉ አስቀድሞ ተነግሮን ስለነበር ጥቃቱን ለመፈጸም በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተን ነበር ሲሉ አቶ ሀሰን አክለዋል

በዜናው ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው አስተያየት የለም።

ከወራት በፊት አርቲስቶችና ጋዜጠኞች የኦጋዴንን የጸጥታ ሁኔታ እና የልማት እንቅስቃሴ እንዲገመግሙ ተልከው እንደነበር ይታወቃል።