(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2011)የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የትላንቱ ጉባዔ የኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው ሲል አስታወቀ።
በትላንቱ ጉባዔ ድል ኮሚቴው ምስጋናውን ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ አቅርቧል።
የኮሚቴው አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ለኢሳት እንደገለጹት የኢትዮጵያ ሙስሊም ለዓመታት ሲጠይቅ የነበረውን በአግባቡ ምላሽ ያገኘበት ጉባዔ ሆኖ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትም ከአዲሱ የዑለማ ምክር ቤትና ቦርድ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ በመግለጽ ህዝበ ሙስሊሙ የትላንቱ ድል እንዳይጨናገፍ እጅ ለእጅ በመያያዝ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አድርገዋል።
በአዲስ አበባ ሚያዚያ 23 የተካሄደውና ታሪካዊ የተባለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉባዔ የኢትዮጵያን እስልምና ታሪክ ወሳኝ ምእራፍ ላይ ያደረሰ ሲል ገልጿል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ።
ትላንት ለዘመናት የጠበቅነው ድላችን ደጃፋችን ላይ እንደደረሰ ምልክት ያረጋገጥንበት ዕለት ነው ያለው ኮሚቴው ለዚህ ውጤት መስዋዕት የሆኑትንና በትግሉ ወቅት አብረው የተሰለፉትን በሙሉ አመስግኗል።
በትግላችን ወቅት ከጎናችን የቆማችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለወደፊቱም ከጎናችን እንድትሆኑ እየጠየቅን ለዛሬው ቀን ስለበቃን እንኳን ደስ አላችሁ ልንል እንወዳለን ያለው ኮሚቴው መንግስትም ለዛሬዋ ቀን እንድንደርስ ላደረገው ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን ብሏል።
ለወደፊቱም የሚጠበቅበትን ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪያውን አቅርቧል ኮሚቴው።
የኮሚቴው አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ለኢሳት እንደገለጹት የትላቱ ጉባዔ ታሪካዊ ነው፡፡ ደስታውም የመላ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የዘመናት ጥያቄ ትላንት ምላሽ አግኝቷል የሚሉት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የሃይማኖቱ ስርዓት በሚፈቅደውና ህዝበ ሙስሊሙ በመረጠው መንገድ በሚዋቀር አካል ለመመራት የተደረገው ተጋድሎ ፍሬ አፍርቷል ብለዋል።
የትላንቱ ጉባዔ መሰረት የተጣለበት ነው ያሉት ኡስታዝ ካሚል ሸምሹ ታሪካዊም አስተማሪም ጉባዔ ሲሉ ገልጸውታል።
በቀጣይ የተቋቋመው ኮሚቴ ስራውን በሚገባ እንዲያከናውን ህዝበ ሙስሊሙ ከጎኑ እንዲቆም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጥሪ አድርጓል።
እንዳለፈው በሹመት የሚሰጥ ሳይሆን የሃይማኖቱን ህግና ስርዓት ጠብቆ በሚከናውን መልኩ የሚደራጅ የሙስሊም ተቋም እንደሚኖር የገለጹት የኮሚቴው አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ይህ ድል እንዳይቀለበስ ሁሉም ነቅቶ መጠበቅና ሃይማኖታዊ ግዴታውን መወጣት አለበት ብለዋል።