የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ጥራት ደረጃ ሊሻሻል አለመቻሉ ተገለጸ

ነሃሴ ፳፬(ሃያ አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዛሬው እለት 3ኛው የአማራ ክልል ትምህርት ፊስትቫል ምክትል ጠቅላይ ሚነስትሩ አቶ ደመቀ መኮነን ፤የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሺፈራው ሺጉጤ ፤ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ በተገኙበት ሲከፈት፣ ዶክተር ጸሐይ ጀምበሬ ባቀረቡት ጽሁፍ፣ የመንግስት ትምህርት ቤት አሰተዳደራዊ ችግር ለትምህርት ጥራት እንቅፋት እየሆነ መጥቱዋል ብለዋል።  ከአመቱ ውስጥ  260 ቀናት ይባክናሉ ያሉት ዶክተር ጽሐይ ኢትዮጵያ በትምህርት ጥራት ደረጃም ከአፍሪካ ሐገራት በዝቅተኛ ደረጃ  ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል። በተለይ ለቌንቌ ትምህርት የተሰጠው ትኩረት እጅግ አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ዶክተሯ፣  የትምህርት ፖሊሲው የአማረኛ ቌንቌ ስነ ልሳን እድገት እንዲቀጭጭ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ልጆቻችንን እንደ ባለስልጣናትና እንደ ሀብታም ልጆች በግል ትምህርት ቤቶች ልከን ማስተማር አንችልም ፣ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚሰጡት ትምህርት ጥራት የለውም ያሉት ወላጆች ፣ መንግስት ለትምህርት ጥራት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

መምህራኑ የ 1 ለ 5 አደረጃጀት ፤ የልማት ቡድን ስራዎች ፤ የፖለቲካ የገጠር ተልኮዎች በትምህርቱ ጥራት ላይ ጫና መፍጠራቸውን ይናገራሉ፡፡  ሌላው ወረቀት አቅራቢ ዶክተር ባይሌ ዳምጤ የሐገሪቱ አመራሮች ከሳይንሳዊነት ይልቅ የአርባ ቀን እድላቸውን የሚያመልኩ፣  የሐገሪቱ መሰረታዊ እውቀት እና ጥበብ የራቀቸው መሆኑን ተንትነው አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ ” አብዮታዊ ዴሞክራሲን በየኒቨርስቲዎች ማስረጽና ማስቀጠል” በሚል ዓላማ  በዩኒቨርስቲ አመራሮች እና በኢህአዴግ መሪዎች መካከል በአዲስ አበባ በተደረገው ውይይት ላይ አቶ በረከት ስምኦን ‘ አገሪቱ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው፣ የምትታደጉን አሁን ነው” በማለት ለምሁራኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በ2011/2012 ብቻ 400 የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት መምህራን ወደ ውጭ ሐገር ለትምህርት ሂደው በተለያየ ምክንያት ጥገኝነት ጠይቀው በዚያው ቀርተዋል፡  ጅማ ፤ መቀሌ እና ባህር ዳር ዩኒቨርስቲዎች በምሁራን ፍልሰት ቀዳሚውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ 673 ከፍተኛ ልምድ ያላቸው መምህራንም ስራቸውን ጥለው ወጥተዋል።  በቂ  ክፍያ ያለመኖር ፣ የፖለቲካ ጫናዎች መበራከት፣  ከትምህርት ጥራት ይልቅ ለትምህርት ሺፋን ትኩረት መስጠት ፤ መምህራን ያለ እምነታቸው  በግዳጅ የሚፈጽማቸው ስራዎች መበራከት ፤ ለመምህራን ፍልሰት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።