በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በስነልቦና ችግር እየተሰቃዩ መሆኑን ተገለጠ

ነሃሴ ፳፬(ሃያ አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከኢትዩ -ኤርትራ ግጭት እና ኢትዮጵያ ከሶማሊያው አልሸባብ ጋር ካደረገችው ጦርነት ጋር በተያያዘ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በስነልቦና ችግር እየተሰቃዩ መሆኑን የጦር ሃይሎች ሆስፒታል የስነ ልቦና ህክምና ቡድን መረጃ አመለከተ

ከመዝገብ ቤት የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው ፤ በጦርነቱ ስዓት በተከሰተ ምንነቱ ባልታወቀ የሞራል እና የስነ ልቦና ችግር ከ3 ሺ 500 በላይ ወታደሮች እስከ እብደት  በሚያደርስ በሽታ ተጠቅተዋል።

ሪፖርተራችን በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው አንዳንድ ወታደሮች በአሰቃቂ የእብደት ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ከማህበረሰቡ ተገልለው ተገቢው ህክምና ሳይሰጣቸው በስቃይ ላይ ይገኛሉ።

ዘጋቢያችን አንዳንድ የወታደር ቤተሰቦችን አነጋግሮ ባጠናከረው መረጃ መንግስት  አካላቸውን ላጡ ሰዎች የ5000 ብር ክፍያ ከመፈጸም ባሻገር ለአዕምሮ ተጎጅዎች  ምንም ዐይነት ክፍያ አላዳረገላቸውም።

የኢሳት ዘጋቢ እንደሚገልጸው ትክክለኛ የመረጃ አያያዝ ዘዴ ቢቀየስ የስነ አእምሮ ተጎጂ ወታደሮች ቁጥር ከተገለጸው አሀዝ በብዙ እጅ ሊልቅ ይችላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህወሐት ነባር ታጋዮችን የሚያሰባሰብ  ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ህወሐትን አሰናፊ ለማድረግ  ከፍተኛ ስራ የሰሩ በተለያዩ የትግራይ  እና በሐገሪቱ ክልሎች የሚገኙ ታጋይ የህወሐት ተወላጆችን ለመደገፍ በማሰብ የህይወት ታሪካቸውን የሚሞሉበት ፎርም በሐገሪቱ ባሉ የፖለቲካ ቢሮዎች መበተኑ ታውቋል።