የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበር አቋርጠው ሶማሊያ መግባታቸው ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 23/2010) ከባድ መሳሪያ የታጠቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበር አቋርጠው ሶማሊያ መግባታቸው ታወቀ።

ለቪኦኤ የሶማሌኛው አገልግሎት ምስክርነታቸውን የሰጡ የዶሎ ከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት አውቶማቲክ መሳሪያዎች በተጠመደባቸው ፒካፖች ታጅበው የሶማሊያን ድንበር አቋርጠው የገቡት የኢትዮጵያ ወታደሮች በቁጥር አንድ ሺ ይገመታሉ።

በትንሹ በ30 ተሽከርካሪዎች ተጭነው ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ድንበር አቋርጠው ሶማሊያ የገቡት የኢትዮጵያ ወታደሮች በአልሻባብ ላይ የሶማሊያ መንግስት ለመክፈት ላቀደው መጠነ ሰፊ ዘመቻ ድጋፍ ለመስጠት እንደሆነ የጌዶ ዞን ገዢ መሐመድ ሑሴን አልቃዲ ለቪኦኤ ሶማሌኛው አገልግሎት ተናግረዋል።

በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ አሚሶም ስር ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች መኖራቸው ይታወቃል።

ይህ በ30 ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ማክሰኞ ምሽት ላይ የሶማሊያን ድንበር አቋርጦ የገባውና አንድ ሺ የተገመተው የኢትዮጵያ ሰራዊት ከአሜሶም ውጭ የሚንቀሳቀስ መሆኑም ተመልክቷል።

የሶማሊያ መንግስት እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 14/2017 በሞቃዲሾ የደረሰውንና ከ300 ሰው በላይ ያለቀበትን አሰቃቂ የሽብር ጥቃት ተከትሎ ሶማሊያን ከአልሻባብ ነጻ የማውጣት ዘመቻን አላማ ያደረገ ነው።

የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናትም በባህረሰላጤው ቀውስ ሳቢያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት ፈተው አልሻባብን በጋራ መመከት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየመከሩ መሆናቸውም ተሰምቷል።

በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣና የፖለቲካ አፈና እንዲቆም አሜሪካ የራስዋን ጫና እንድታደርግ በአሜሪካ ምክር ቤት የቀረበውና ኤች አር 128 የተባለው ሕገ ውሳኔ በምክር ቤቱ ከጸደቀ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ከሶማሊያ እንደምታስወጣ የኢትዮጵያ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።

ሆኖም ሕገውሳኔው በሂደት ላይ እያለ ተጨማሪ ወታደር መላኳ ግልጽ አልሆነም።