የካታላን መሪዎች ዛሬ ስፔን ማድሪድ ፍርድ ቤት ቀረቡ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 23/2010)ካታላንን ከስፔን በመገንጠል ነጻ ሀገር መሆኗን ያወጁት የካታላን መሪዎች ዛሬ ስፔን ማድሪድ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ከፕሬዝዳንቱ ጋር ወደ ቤልጂየም ከተሰደዱት 6 ሚኒስትሮች ሁለቱ ወደ ስፔን መመለሳቸው ታውቋል።

ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ አራቱ ሚኒስትሮች ተላልፈው እንዲሰጡት የስፔን መንግስት ይጠይቃል ተብሎም እየተጠበቀ ነው።

የካታላን ምክትል ፕሬዝዳንት ኦሪዮ ጆንኩራስን ጨምሮ ዛሬ ማድሪድ ብሔራዊ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የካታላን ከፍተኛ ባለስልጣናት በእምነት ማጉደል፣በመንግስት ላይ በማመጽና አመጽ ማደራጀትን ጨምሮ በርካታ ክሶች ቀርበውባቸዋል።

በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙም እያንዳንዳቸው የ30 አመት እስራት ይጠብቃቸዋል።

ክስ የተመሰረተባቸው ባለስልጣናት ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ 28 እንደሆኑም ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር አርብ ጥቅምት 27/2017 የተጀመረውን የካታላንን የነጻነት ጥያቄ በማገድ እንዲሁም የቀድሞውን የራስ ገዝ በመሰረዝ ግዛቲቱን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው የስፔን መንግስት በመጪው ታህሳስ አዲስ ምርጫ ተካሂዶ መሪዎች እስኪሰየሙ ጊዜያዊ ባለስልጣናትን ሾሟል።

ምርጫውም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 21/2017 እንዲካሄድ መርሃ ግብር ተነድፏል።