ነኅሴ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ሂራን ክልል ውስጥ ከአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ጦር፣ አሚሶም ተልኮ ውጪ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የአሚሶም ምድብ አራት የጦር አዛዥ የሆኑት አብዱራህማን አብዲ ዲምቢሊ ቅሬታቸውን አሰሙ።
ጅቡቲያዊው የጦር አዛዥ ኮማንደር አብዱረህማን ፣ ካለ ህብረቱ ጦር ትእዛዝ በሂራን ግዛት የኢትዮጵያ ወታደሮች አልሸባብን ደምስሰው አካባቢውን ከተቆጣጠሩት በኋላ ለሶማሊያ መንግስት ወታደሮች አስረክበው እነሱ በመልቀቃቸው አልሸባብ የተነጠቃቸውን አካባቢዎች ድጋሚ ተቆጣጥሮታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአሚሶም መመሪያ ውጪ ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ ቀጥታ ይቀበላሉ ፣ ይሄም በሰላም ተልኮው ላይ ትልቅ ሳንካ ፈጥሯል ሲሉ አዛዡ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጦር አላማ ምን እንደሆነ በግልጽ እንዲነገራቸው፣ ህብረቱ ግፊት ማድረግ እንዳለበትም አዛዡ አክለው ግልጸዋል። የጅቡቲው የጦር አዛዥ ያነሱት ጥያቄ፣ ከፍተኛ ሰራዊት ለአሰማራው የኢህአዴግ መንግስት፣ የሚዋጥ አይሆንም።