(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 15/2010) በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የአክቲቪስት ገዛሀኝ ገብረመስቀልን ግድያ የግል መርማሪ ቀጥሮ ሊያሰራ መሆኑ ታውቀ።
ባለፈው ቅዳሜ በጥይት ተመቶ በተገደለው የአክቲቪስት ገዛሀኝ/ነብሮ/ አሟሟት ኢትዮጵያውያን ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።
ግድያው በህወሃት ኤምባሲ በኩል መፈጸሙን የሚያሳዩ ፍንጮች እንዳሉ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሰብሳቢ ለኢሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ ገልጸዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባል ሆኖ ሀገሩን ከአደጋ ለማዳን በዱር በገደሉ ተዋግቷል።
በልጅነቱ የተሸከመው ሀገራዊ ሃላፊነትና አደራ በመንግስት ለውጥም የሚዘነጋው አልነበረውም።
በስደት በሚኖርባት ደቡብ አፍሪካ እሰክሕይወት ዋጋ ሊከፍልላት ቃል ለገባላት ሀገሩ የሚችለውን ሁሉ ሲያደርግ የኖረ፣ ከሚወደው ሰንደቅዓላማ ሳይለይ ለ27 ዓመታት በደቡብ አፍሪካ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ጉዳይ ከተነሳ ምንጊዜም ከፊት ቀድሞ የሚገኝ ነው። አክቲቪስት ገዛሀኝ ገብረመስቀል ወይም በቅጽል ስሙ ነብሮ።
ባለፈው ቅዳሜ በሚኖርበት የደቡአፍሪካ ጆሀንስበርግ ከተማ በአንድ ወጣት በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ አልፏል።
ህዝብ በተሰበሰበበት መናፈሻ አካባቢ በተቀመጠበት ቦታ ተጠግቶት የገደለው ደቡብ አፍሪካዊ እስከአሁን አልተያዘም።
ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረው ሲሆን የግድያው ምክንያት በፖሊስ ይፋዊ ምላሽ አልተሰጠውም።
በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ከግድያው ጀርባ የህወሃት አገዛዝ እንደሚኖርበት ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሰብሳቢ አቶ ታምሩ አበበ ለኢሳት ሲገልጹ ጉዳዩ ምንም እንኳን በምርመራ ላይ ያለ ቢሆንም ግድያው በህወሃት ኤምባሲ አማካኝነት ለመፈጸሙ እርግጠኛ ነኝ በማለት ነው።
ኢሳት የግድያውን መንስዔ ለማጣራት እየሞከረ ሲሆን ያነጋገርናቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን በህወሀት የእጅ አዙር ጥቃት የአክቲቪስት ገዛሀኝ ህይወት እንደጠፋ ይናገራሉ።
አቶ ታምሩ አበበ ዛሬ በአስከሬን ምርምራ ክፍል በመገኘት የአክቲቪስት ገዛህኝን አስክሬን መመልከታቸውን በመግለጽ በአንገቱ ላይ ተጠግቶ እንደተመታና ይህም በፕሮፌሽናል የግድያ ስልት አንድ ሰው እንዳይተርፍ ተደርጎ ለመግደል የሚጠቀሙበት ዘዴ መሆኑን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ላይ ገልጸዋል።
አክቲቪስት ገዛህን በተደጋጋሚ የግድያ ዛቻ ከህወሀት በኩል እንደሚደረሰው የገለጹት አቶ ታምሩ ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ የግድያ ሙከራ ተደርጎበት ማምለጡን ይናገራሉ።
ይህን ጉዳይ በቀላሉ የምናየው አይደለም፣ ጦርነቱን ደጃፋችን ድረስ ይዘው ከመጡ አጸፋውን ለመመለስ አያቅተንም ያሉት አቶ ታምሩ በወንድማችን ግድያ አንገታችን ተሰብሮ የምንቀር ሳይሆን በእልህና ቁጣ አጸፋውን ለመስጠት የምንዘጋጀበት ነው በማለትም በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥሪ አድርገዋል።
በአሁኑ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ምርመራውን እያካሄደ ሲሆን ጉዳዩ የደቡብ አፍሪካንም ሉአላዊነት የሚነካ በመሆኑ ላቅ ባለ የምርመራ ደረጃ እንዲከናወን ግፊት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አቶ ታምሩ አበበ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ምርመራውን የግል መርማሪ በመቅጠር ለማከናውን ዕቅድ መያዙን የገለጹት አቶ ታምሩ ለዚህ የሚያስፈልገውን ወጪ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይሸፍኑታል ብለው እንደሚጠብቁም ጠቅሰዋል።
አክቲቪስት ገዛሀኝ ድንገት ከእናንተ ቀድሜ ብሞት ህወሃት ወደሚቆጣጠራት ኢትዮጵያ አስከሬኔን እንዳትልኩት በማለት ቃል ስላስገባን የቀብር ስነስርዓቱ በደቡብ አፍሪካ ይፈጸማል ብለዋል የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሰብሳቢ አቶ ታምሩ አበበ።
ባለቤቱንና ኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተሰቦቹን በማነጋገር በዚህ ሳምንት መጨረሻ የቀብር ስነስርዓቱን በደቡብ አፍሪካ እንደሚፈጸምም አቶ ታምሩ ገልጸዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዝምታን መምረጡ ደግሞ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።