የኢትዮጵያ እና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተወያዩ

ሰኔ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የኢትዮጵያና የግብጽ ፍጥጫ እያየለ መምጣቱን ተከትሎ የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሞሀመድ ካሚል በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ጋር ተነጋግረዋል።

ሬዲዮ ፋና ባቀረበው የቀን ዘገባ ላይ  የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት ባደረጉት የማለዳው ውይይት ከስምምነት ላይ ሳይደርሱ መቅረታቸውን ገልጿል። ሬዲዮ ፋናም ሁለቱ ባለስልጣኖች ስምምነት ላይ አልደረሱም የሚል ዜና ይፋ ካደረገ በሁዋላ ወዲያውኑ ዜናውን ሰርዞታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ  ውይይት ከሰዓት  የቀጠለ ሲሆን የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ውይይቱ የተሳካ መሆኑን፣ የቃላት ጦርነቱን ለማቆም መስማማታቸውንና ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ተጨማሪ ጥናት እንዲካሄድ መፍቀዷን” መናገራቸውን የግብጽ የመገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል   ።

ግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን በ1929 እና1959 በተደረጉ ውሎች መሰረት የዓባይን ውሃ በበላይነት  መጠቀም አለብኝ ስትል፣ ኢትዮጵያና  ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ደግሞ  የተጠቀሱት ውሎች  ፍትሀዊ አጠቃቀምን  መሰረት ያላደረጉና ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው ይላሉ።

ባለፈው ሳምንት የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው የነበሩት ግብጽና ኢትዮጵያ  ፊታቸውን ወድ ዲፕሎማሲው መንገድ በመመለስ ለመወያት ቢሞክሩም፤ ከያዙት የተራራቀ ሀሰብ አንፃር ወደ ስምምነት ሊደርሱ ይችላሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

ኢሳት ባለፈው ሳምንት እንደዘገበው በግብጽ በኩል እየቀረበ ያለው አዲሱ መከራከሪያ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ግድቡ የሚይዘው የውሀ አቅም ይቀነስ የሚል ነው።