በአፋር የገዋኔ ነዋሪዎችና በፌደራል ፖሊሶች መካከል ያለው ውዝግብ እንደቀጠለ ነው

ሰኔ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ትናንት ገዋኔ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ አንድ ሾፌር መገደሉን ተከትሎ በፖሊሶች እና በነዋሪዎች መካከል አዲስ ውዝግብ ተከስቷል። በአካባቢው የተሰማሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት ለሹፌሩ መገደል የገዋኔ ነዋሪዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

ነዋሪዎቹ በበኩላቸው ግድያውን የፈጸሙት እነሱ አለመሆናቸውን  የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሀይሰማ ወልዶ እና ሌሎች ሁለት የፌደራል ፖሊስ አዛዦች በተገኙበት ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ “የፌደራል ፖሊስ አባላት ሶስት ጊዜ ተኩስ ከፍተውብናል” በማለት አቤቱታ ያሰሙ ሲሆን፣ ተገደለ የተባለውንም ሾፌር እነሱ አለመግደላቸውንና  ፖሊስ ራሱ በእነሱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ብሎ ያቀነባበረው መሆኑን ገልጸዋል።

ሰኔ 1 ቀን 2005 በገዋኔ ወረዳ ሌአስ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ በፌደራል ፖሊሶች ፊት አንድ  ሙሀመድ አዩብ የተባለ ጎልማሳ መገደሉ ይታወቃል።  ግድያውን ተከትሎም በነዋሪዎች እና በፌደራል ፖሊስ አባላት መካከል የተነሳው ውዝግብ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ እያለ ቀጥሏል።