የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መጅሊስ ፕሬዝዳንት ስልጣን ለቀቁ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 21/2011)በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ህገወጥ ነው በሚል ሲወገዝ የነበረው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መጅሊስ ፕሬዝዳንት ከስልጣን መልቀቃቸው ተገለጸ።

ፕሬዝዳንቱ ሼህ መሀመድ አሚን ጀማል እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ መልቀቂያ በማስገባት ከስልጣን በገዛ ፈቃዳቸው መነሳታቸው ታውቋል።

ምክር ቤቱ እንዳስታወቀው ሼህ መሀመድ በጤና ችግር ምክንያት መቀጠል አልቻሉም።

ለአራት ዓመታት በዘለቀው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞ መነሻ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ህገወጡ መጅሊስ ይፍረስ የሚል እንደነበረ ይታወሳል።

የሼህ መሀመድ አሚን ከስልጣን መነሳት በቂ አይደለም ፣ መጅሊሱ የእምነቱን ስርዓት ጠብቆ መዋቀር አለበት ሲሉ የሃይማኖቱ አዋቂዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

የቢቤኢን ሬዲዮ አዘጋጅ ሳዲቅ አህመድ በመንግስት የተሰየመው መጅሊስ እስካልተቀየረ ድረስ ፕሬዝዳንቱ መነሳት ለውጥ አይመጣም ሲል ለኢሳት ገልጿል።