የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚያደርገውን በረራ አቋራጠ

ሚያዚያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚያደርገውን በረራ አቋራጠ የደቡብ ሱዳን መንግስት ተቃውሞውን ቀጥሎአል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ኦፊሴላዊ የጉዞ ማመላለሻ መሆኑ በተነገረ በወራት ውስጥ፣ ወደ አገሪቱ ዋና ከተማ ጁባ እና ወደ ማላካ የሚደረገው በረራ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ጁባ ከሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመደወል ለማረጋጋጥ እንደተቻለው ሰራተኞቹ ወደ ጁባና ሌላዋ የደቡብ ሱዳን ከተማ ወደሆነቸው ማላካ ምንም አይነት ትኬት እንዳይቆርጡ፣ ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል። ለሰራተኞቹ በምክንያትነት የተገለጸላቸው የጸጥታ ችግር የሚል ነው። አቶ መለስ አየር መንገዱ በረራ እንዲያቋርጥ ያዘዙት ፤ ሁለቱን አገሮች ለማስታረቅ መንግስታቸው የጀመረው ጥረት ሊሳካ አለመቻሉ ስላበሳጫው ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ። አቶ መለስ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናትን ዘልፈዋቸው እንደነበር የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት አየር መንገዱ በረራውን በማቋረጡ ለኢትዮጵያ መንግስት አቤቱታ አቅርቧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካርቱም የሚያደርገውን በረራ ሳይሰርዝ ወደ ጁባ የሚያድረገውን በረራ መሰረዙ ፖለቲካዊ ተቀባይነት አይኖረውም ብሎአል። አቶ መለስ በግልጽ የአልበሽር ደጋፊ ሆነው መውጣታቸው እየተነገረ ነው። ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር የሚፋለመውን የደቡብ ሱዳን አማጽያንንም እንደሚረዳ ሚስጢራዊ መረጃዎች አመልክተዋል። ጄኔራል አልበሸር ጦራቸው ጁባ ድረስ በመሄድ ደቡብ ሱዳንን የሚያስተዳድረውን የኤስ ፒ ኤል ኤም አመራሮችን ከስልጣን እንደሚያወርዱ ዝተዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ ካፒታል ኤኢ.ኤም እንደዘገበው፤ የሱዳን መንግሥት ዜጎቹ ከደቡብ ሱዳን ጋር ለሚደረገው ጠቅላላ ጦርነት እንደሚመለመሉ አስታውቋል ::
በኬንያ የሱዳን አምባሳደር ከማል እስማኤል ሰዒድን ዋቢ ያደረገው ይኸው የ ካፒታል ኤፍ. ኤም ዘገባ፣ በነዳጅ ዘይት ምክንያት በተባባሰው ውጥረት ምክንያት የደቡብ ሱዳን ወታደሮች ከአካባቢው ካልወጡ፤ የአልበሽር መንግስት ማናቸውንም ዓይነት ዋጋ ከፍሎ ጦርነት የመጀመር አቋም ላይ ደርሷል::

“እንደ ነፃ አገር ሱዳን ራሷን መከላከል ትችላለች” ያሉት አምባሳደር ከማል፤ “ጦርነት ከተጀመረም ጠቅላላ ሕዝቡ እስከመጨረሻው ይዋጋል” ሲሉ ተደምጠዋል::
“ይህ የመደበኛው ሠራዊት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ በሁሉም የሙያ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ጉዳይ ነው። ስለሆነም ፤ሁሉም ሱዳናውያን
በውጊያው ላይ ይሰለፋሉ” በማለት መንግስታቸው የቀድሞ አካሉ በነበረችው በጁባ ላይ ሁሉን አቀፍ ክተት ለማወጅ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል-አምባሳደር ከማል።
አክለውም፦” አገራችን ወደ ጦርነት ለመግባት ፍራቻ የላትም !ደቡብ ሱዳኖች ከአወዛጋቢው ስፍራ እስኪወጡ ድረስም ውጊያው ይቀጥላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል::
የነዳጅ ዘይት እምብርት ተብላ በምትጠራው “ሔግሊግ” ከተማ ባለፈው ቅዳሜ የሱዳን አየር ኃይል በፈጸመው ድብደባ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ዓለማቀፍ ብዙሀን መገናኛዎች ዘግበዋል::
__________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide