የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከ 31 ዓመት በሁዋላ ለአፍሪካ ዋኝጫ ውድድር አለፈ

ጥቅምት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መንግስት የብሔራዊ ቡድኑን ውጤት የፖለቲካ መነገጃ ለማድረግ መሞከሩ ብዙዎችን ቅር አሰኝቷል።

በቅጽል ስሙ<ዋሊያ>ተብሎ የሚጠራው የ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሱዳን አቻው ጋር ትናንት በ አዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገው የመልስ ጨዋታ ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ነው ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ማለፉን ያረጋገጠው።

ከወራት በፊት ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ አንድ ላይ ሲመደቡ፤ በሁለቱም አገሮች ዘንድ የደስታ ስሜት ተፈጥሮ ነበር።

የደስታ ስሜቱ በሁለቱም ዘንድ የተፈጠረው፤ አንድኛቸው ሌለኛቸውን ማሸነፍ እንደሚችሉ   ሁለቱም በየፊናቸው ተስፋ በማድጋቸው ነበር።

ካርቱም ላይ በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ የሱዳን ብሔራዊ ቡድን  5 ለ 3 በማሸነፍ ተስፋውን  አሰፋ።

በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ 5 ለ 3 የተሸነፈው ብሔራዊ ቡድናችን ከሴካፋ ተሻግሮ  ወደታላቁ የ አፍሪካ ዋኝጫ  ውድድር ለማለፍ የትናንቱን ጨዋታ በሁለት ጎል ልዩነት ማሸነፍ ግዴታው ነበር።

የ አፍሪካ እግር ኳስ መስራች የሆነችው አገር ለሦስት አስርት ዓመታት ከአፍሪካ ዋንጫ ውድድር  ርቃ መቆየቷ ሲያብነክነውና ሲያስቆጨው የኖረው ስፖርት አፍቃሪው ህዝብ የ አዲስ አበባ ስታዲየምን ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላው፤ ገና ውድድሩ ከመጀመሩ ከ ሰዓታት በፊት ነበር።

ጨዋታው እንደተጀመረ የ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  በሱዳን አቻው ላይ ጫና ፈጥሮ መጫዎት መጀመሩ፤  ግጥሚያውን በተፈላጊው ውጤት  ያሸንፋል የሚል ተስፋ ቢያሳድርም፤ ረዥም ኳስ መጫዎት መምረጣቸው፤እንዲሁም ሱዳኖች ከ 20 ደቂቃ በሁዋላ  ፍጥነታቸውን በመጨመር ኳስን መቆጣጠር በመጀመራቸው፤ እንግዳው ቡድን ባገኘው ቀዳዳ ተጠቅሞ አንድ ጎል በማስቆጠር የብሔራዊ ቡናችንን ዕዳ ወደ 3 ጎል እንዳያሳድገው የሚል ስጋት መፈጠሩ አልቀረም።

ይሁንና የመጀመሪያ 45 ደቂቃ ያለ ምንም ጎል ተጠናቀቀ።

ኢትዮጵያ 2 ጎል ለማስገባት የነበራት 90 ደቂቃ በግማሽ ዝቅ ብሎ 45 ደቂቃዎች ቀሩ። በ አረንጓዴ፣ቢጫ እና ቀይ መለያ የተዋቡት ዋሊያዎች  የተጣለባቸውን የሚሊዮኖች ሀላፊነት በብቃት ለመወጣት በሙሉ እልክና ወኔ ተመለሱ።

ሁለተኛው 45 ደቂቃ  መጀመሩን የሚያውጀው የሴኔጋላዊው ዳኛ ፊሽካ ጮኸ።

ዋልያዎች ተቃራኒውን ቡድን ፋታ ባለመስጠትና ከፍተኛ ጫና በመፍጠር፤ በማጥቃት ላይ የተመሰረት ጨዋታቸውን አቀጣጠሉ። በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ ሶስት የማዕዘን ምቶችን እስኪያገኙ ድረስ የበላይነታቸው በግልጽ እየታዬ መጣ።

ለካርቱሞች ራስ ምታት ሆኖ የዋለውና፤ በተደጋጋሚ ጎል ላይ እየደረሰ ያደረጋቸው አስደንጋጭ ሙከራዎች አንዴ በአግዳሚው የጎል ብረት፤ ሌላ ጊዜ በጎል ጠባቂው የከሸፈበት የፊት መስመሩ ፊታውራሪ አዳነ ግርማ ከ ቀኝ ክንፍ በኩል የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በጭንቅላቱ በመግጨት ከመረቡ ጋር አዋደዳት። እርጅና የተጫጫነው የአዲስ አበባ ስታዲየም በጭፈራና በዕልልታ አረገረገ።

ብዙም ሳይቆይ ተቀይሮ የገባው አዲስ ህንፃ ከግራ በኩል በረዥሙ የመታትን ኳስ ለማግኘት አዳነ ግርማና አንድ የሱዳን ተከላካይ ሲታገሉ ፤ ኳስ በወዳጇ በሳልሀዲን እግር  ላይ ወደቀች።   ፈጣኑና  ቆፍጣናው ሳልሀዲንም  በፍጥነት በመምታት፤ በደቡብ አፍሩካ ለሚካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አገሩ ትኬት የቆረጠችበትን ወሳኝ ጎል አስቆጠረ።

አዳነ ግርማ  ለእንግዶቹ  አንድ ብሎ  የጀመረውን የጎል ግብዣ ሳላሀዲን፦”በባህላችን መሰረት አንድ ያጣላል” በማለት ሁለተኛውን ደገማቸው።

ይህ ውጤት እንደተጠበቀ ሁለተኛው ግማሽ ተጠናቀቀ።

የኢትዮጵያ- ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ምኞትና ጉጉት ከ 31 ዓመታት በሁዋላ ዕውን ሆነ።

 

<<ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም>> በሚል ዜማ ከስታዲየሙ ጫፍ እስከ ጫፍ ተስተጋባ። ዋልያዎች በጨዋታ ብቻ ሳይሆን በብልጠት ጭምር በልጠው፤ የፎከሩባቸውን ሱዳናውያን አንቀጥቅጠው  በማሸነፍ ለታላቁ ውድድር አለፉ።

ይህም በየትም ስፋራ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ደስታን ፈጥሯል።

በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ራዲዮ ድርጅት ብሔራዊ ቡድናችን የተቀዳጀውን ድል አስመልክቶ  የተሰማውን ታላቅ ደስታ በአድማጮቹና በተመልካቾቹ ስም ለኢትዮጵያ ህዝብ ይገልፃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢህአዴግ  የብሔራዊ ቡድኑን ውጤት የፖለቲካ መነገጃ ለማድረግ መሞከሩ በርካታ ስፖርት አፍቃሪ ኢትዮጵያውያንን እያስቆጣ ይገኛል።

ብዙዎች ቁጣቸውን እየገለጹ ያሉት ፤ የመንግስት ብዙሀን መገናኛ <<የብሄራዊ ቡድኑ ድል መታሰቢያነቱ ለአቶ መለስ ነው>> የሚል ቅስቀሳ መጀመራቸው ነው።

ከኢትዮጵያ አልፈው ለአፍሪካ እግር ኳስ  ታላቅ ተጋድሎ የፈፀሙትን  እነ ይድነቃቸው ተሰማን  ባፈራች አገር የተገኘው የኳስ ድል፤በ 21 ዓመት የስልጣን ቆይታቸው አንድ ጊዜ እንኳ ሳት ብሏቸው ስታዲየም ገብተው ኳስ ጨዋታ አይተው ለማያውቁ ሰው መታሰቢያ ይሁን መባሉ፤ በጣም አስቂኝ፣ አሳዛኝም ነው ብለዋል-በርካታ ስፖርት አፍቃሪዎች በማህበራዊ መገናኛዎች በሰጧቸው አስተያዬቶች።

በሰማንያዎቹ አጋማሽ አካባቢ ስለስታዲየም ግንባታ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መለስ፦<<ስታዲየም የምንሰራበትን ገንዘብ ማዳበሪያ እንገዛበታለን>> ማለታቸው ይታወሳል።

እንዲሁም የ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካይሮ ሂዶ ከግብጽ አቻው ጋር ባደረገው ግጥሚያ 6 ለ 1 በተሸነፈበት ወቅት በዚያው ስለከዱት 6 ተጨዋቾች ሲጠየቁ ፦<ገበሬ ቢከዳ ነበር የሚቆጨኝ>ማለታቸው አይዘነጋም።

ብዙዎች በፌስ ቡክ በሰጡት አስተያዬት<< አቶ መለስና እግር ኳስ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በጥሩ ባልተያዩበት፤ሌላው ቢቀር በ ዓጼ ሀይለስላሴ  ለተሠራው ለአዲስ አበባ ስታዲየም የእድሳትና የማስፋፋት ሥራ ባልተካሄደበት ሁኔታ ነው የተለያዩት።በዚህ ስቴዲየም ላይ የተደረገ ጨዋታ ድል፤ በምን ስሌት ነው የ እርሳቸው መታሰቢያ የሚሆነው?>>ሲሉ ጠይቀዋል።

<<ምንም ድሉ  ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ ጥርጊያ በር የከፈተ እንጂ የአፍሪካ ዋንጫ የተገኘበት ባይሆንም ፤ኢህአዴግ  ይህን ድል  ለመሪው መታሰቢያ ያደረገው ሀቁ ጠፍቶት ሳይሆን  ልክ እንደ አቶ መለስ ሀዘን  ሁሉ ፖለቲካዊ ንግድ ሊያካሂድበት ስለፈለገ እንደሆነ ገብቶናል >> አሉ ፍኖተ የተባሉ አንድ አስተያት ሰጪ፤ <<ማህበራዊ ተሳትፎዎች በሚበዙባቸው ቦታ ሁሉ ጥልቅ ማለት ፤የገዥው ፓርቲ መለያ በመሆኑ በሁኔታው አልተደነቅኩም>ብለዋል።

ጨዋታውን በ አዲስ አበባ ስታዲየም ተገኝተው ተከታተሉ ኢሳት ዘጋቢዎች አስተያዬታቸውውን የሰጡ በርካታ የ አዲስ አበባ ስታዲየም ተመልካቾችም<<በሀይማኖቱ፣በኪነ-ጥቡ፣ በሀዘኑ፣በ ዕድሩ፣ በትምርት ቤቱ፣በፍርድ ቤቱ ..ጥልቅ  እያለ ያስቸገረን ኢህአዴግ፤ ምናለ እግር ኳሳችንን እንኳ ባይነካካብን፣ለምን በደስታችን ላይ ውሀ ይቸልስብናል?>>በማለት ነው በድርጊቱ ተቃውሟቸውን የገለፁት።