ታህሳስ 04 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- “ቡና በብትን መልክ ብቻ ለማዕከላዊ ገበያ ይቅረብ” የሚለው መመሪያ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና ገዥ የሆኑ አስር የውጭ አገር ኩባንያዎችና ማህበራት በብትን መልክ የሚቀርበውን የኢትዮጵያን ቡና እንደማይገዙ አሳወቁ።
ገዥ በማጣት አጣብቂኝ ውስጥ የወደቁትና መመሪያው እንዲቀየር ለንግድ ሚኒስቴር ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ የተደረገባቸው ቡና ላኪዎች፤ ለአቶ መለስ ዜናዊ አቤቱታ ለማሰማት እየተዘጋጁ ነው።
የኢትዮጵያ ቡና ገዥ ከሆኑት መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱት የስዊዘርላድንና የጀርመን ኩባንያዎች በማኅበሮቻቸው በኩል ለኢትዮጵያ ኤምባሲዎች፣ ለውጭ ጉዳይና ለንግድ ሚኒስቴር የተቃውሞ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡
ሪፖርተር እንዳለው፤የእንግሊዝ ኩባንያዎችን ጨምሮ አሥር ታዋቂ የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙ ማኅበራት በብትን መልክ እንደማይገዙ ያሳወቁ ሲሆን፣ ፊታቸውን ወደ ሌሎች ቡና ሻጮች ማዞራቸውም እየተነገረ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የኮሎምቢያና የኬንያ ቡና ላኪዎች የአረቢካ ቡና ገበያን ሊቆጣጠሩት እንደቻሉ፣ በዚህ ሳምንት ብቻ ኢትዮጵያ ልትሸጥ የሚገባት 30 ሺሕ ቶን የሚገመት ቡና ሳይሸጥ መቅረቱንም የጋዜጣው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ንግድ ሚኒስቴር ከህዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ያወጣውን መመርያ ቡና ገዥዎች አጥብቀው እንደተቃወሙት ይታወቃል።
“ገዥዎቹ አገራት ፦ ‘ በኮንቴይነር በብትን እንዲላክልን አንፈልግም’ ብለውናል” በማለት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ያቀረቡትን ሐሳብ ንግድ ሚኒስቴር ሊቀበለው ባለመቻሉ፣ ለአቶ መለስ ዜናዊ የአቤቱታ ደብዳቤ ለማቅረብ መገደዳቸውንና የተቃውሞ ደብዳቤያቸውንም በነገው ዕለትም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንደሚያስገቡ ምንጮቹ ጠቁመዋል ፡፡
ከህዳር 1 ቀን ጀምሮ ሁሉም ላኪዎች ቡና በብትን በኮንቴይነር እንዲልኩ የወጣውን መመርያ ቡና ገዥዎች እንዳልተቀበሉት፤ በጆንያ የማይላክላቸው ከሆነ “ከኢትዮጵያ ቡና አንገዛም” ማለታቸውን ላኪዎቹ ለንግድ ሚኒስቴር ዴኤታው በግልጽ ያሳወቁት ባለፈው ሳምንት ነበር።
ሚኒስቴር ዴኤታው ግን የላኪዎቹን አቤቱታ ባለመቀበልና እንዲሁ በደፈናው፦ “አሳምናችሁ በብትን እንዲገዙ አድርጉ” በማለት ነው መመሪያው ሊቀየር እንደማይችል የነገሯቸው።
ከፍተኛ የታጠበ ቡና በጥርና በካቲት ወራት ተጓጉዞ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ አሁን ውል ሊፈጸም ይገባ እንደነበር የሚገልጹት ቡና ላኪዎች፣ አሁን በሚታየው የዓለም የኢኮኖሚ መዋዠቅ የቡና ኤክስፖርት መቀነሱን ይናገራሉ፡፡
ገዥዎች የኢትዮፕያን ቡና “ በብትን አንገዛም” ከማለታቸው ጋር ተያይዞ ቡናው በመጠንና በገቢ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉንና ወደፊትም ከዚህ የበለጠ ሊቀንስ እንደሚችል የገለጹት ላኪዎቹ፤ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ እጅግ የሚጎዳ አሳሳቢ ችግር መፈጠሩንም አልሸሸጉም፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ቡና ራስን በራስ የማጥፋት ዕርምጃ ተወስዶበታል፤›› ሲሉ አንዳንድ የቡና ላኪዎች እየገለጹ እንደሚገኙም ጋዜጣው ዘግቧል።
በ አሁኑ ጊዜ “ቡና በብትን መልክ ብቻ ለገበያ ይቅረብ” የሚለውን የንግድ ሚኒስቴርን መመርያ አስመልክቶ ላኪዎች የተቃውሞ ፊርማ(ፒቲሺን) እያሰባሰቡ መሆናቸውም ታውቋል።