የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲውን አመራሮች መረጠ

03 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ላለፉት ሁለት ቀናት  ጠቅላላ ጉባኤውን ካደረገ በሁዋላ፣ የፓርቲውን ሊቀመንበር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት እና የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላትን መርጧል።

የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን በሊቀመንበርነት የመረጠው ጉባኤ፣ ለብሄራዊ ምክር ቤት ከመረጣቸው 40 ሰዎች መካከል በእስር ላይ የሚገኘውን አቶ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ ዶ/ር ሀይሉ አርአያ፣ ዶ/ር ንጋት አስፋው፣ አቶ አስራት ጣሴ፣ አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ እና አቶ ስዬ አብርሃ ይገኙበታል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ለምክር ቤቱም ሆነ ለተጠባባቂ ምክር ቤት አባልነት አልተካተቱም ።

ጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባውን ሲያጠቃልል ባወጣው መግለጫ፣ ገዢው ፓርቲ ህገወጥ በሆነ መንገድ ያሰራቸውን አመራሮች አቶ አንዱአለም አራጌንና አቶ ናትናኤል መኮንንን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲውን አባላትና የህሊና እስረኞች እንዲፈታ ጠይቋል።

ፓርቲው የመጪውን ዓመታት የትግል ጉዞ የእድሳትና የማንሰራራት ዘመን በማለት ሰይሞታል።

ሰላማዊ ትግል ከፍተኛ የሆነ ጽናትና ትግስት የሚጠይቅ በመሆኑ ፣ ህዝቡን የሉአላዊነቱ ባለቤት ለማድረግ በሚደረገው ትግል አንድነት ግንባር ቀደም ሆኖ እንደሚሰለፍ ገልጧል። ፓርቲው ከመድረክ ጋር ግንባር ለመፍጠር ያደረገውን ስምምነትም ጠቅላላ ጉባኤው አጽድቆታል።

በሌላ በኩል ደግሞ  በስልጣን ላይ ያለውን  ፓርቲ በምርጫ ማስወገድ አይቻልም ሲሉ  ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ተናግረዋል።

ዶ/ር ነጋሶ የቪኦኤ የእንግሊዝኛ ዘጋቢ ከሆነው ፒተር ሄይንላይን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጡት፣ አሁን የተዘረጋው የፖለቲካ ስርአት ምርጫ ለማካሄድ አመቺ ባለመሆኑ ያለው ብቸኛ አማራጭ መንግስትን በሰላማዊ ትግል ማውረድ ነው።

“አምባገነኖች ለረጅም ጊዜ እንደማይኖሩ አይተናል፣ የሆነ ጊዜ ህዝቡ ተነስቶ በቃችሁ ይላል። በዚህ ዓመት ላይሆን ይችላል። በሚቀጥለውም ዓመት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የሆነ ሰአት ላይ ህዝቡ ተቆጥቶ ይነሳል። ለውጥ የሚመጣውም በዚህ መልክ ነው።” ሲሉ ዶ/ሩ አክለዋል።

ኢህአዴግ ኮሚኒስታዊ አስተሳሰቡን አለመተውን የሚናገሩት ዶ/ር ነጋሶ፣ ግንባሩ ራሱን ትክከለኛ እና በቸኛ ሀይል አድርጎ በማስቀመጥ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ ለመቆየት ማለሙንም ጠቁመዋል።

የአንድነት ፓርቲ ሁለት ኮከብ መሪዎቹ በጸረ ሽብር ስም እስር ቤት እንደሚገኙ ይታወቃል።

አንዱአለም አራጌ እና ናትናኤል መኮንን ሰላማዊ ትግሉን ወደ ፊት በመግፋት ገዢውን ፓርቲ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከትተውት እንደነበር ይታወቃል።