የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ስለታሰሩት የሙስሊም አመራሮች የሰጠውን መግለጫ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦችና ሙስሊሞች ተቃወሙት

መስከረም ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአምባሳደር ጥሩነህ ዜና የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን  ከሙስሊሞች መብት የማስከበር እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ስለታሰሩት የሙስሊም አመራሮች የሰጠውን መግለጫ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦችና ሙስሊሞች ተቃወሙት።

ኮሚሽኑ  ከታሳሪዎች  የወንጀል ምርመራ ሀላፊዎች የነገሩትን ቃል እንደወረደ ነው መግለጫ ብሎ የሰጠው።

ከመብት ማስከበሩ ትግል ጋር በተያያዘ የታሰሩት ሙስሊሞች ከ 100 በላይ መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው እየገለጹ ባለበት ሁኔታ፤  ኮሚሽኑ <የታሰሩት 30 ብቻ ናቸው> የሚል መግለጫ ሰጥቷል።

የታሳሪዎች ቤተሰቦች በኮሚሽኑ የተጠቀሰውን አሀዝ እንደማይቀበሉትና፤ ታሳሪዎቹ በኮሚሽኑ ከተጠቀሰው አሀዝ ከሦስት እጥፍ በላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሙስሊሞች መብት የማስከበር ትግል አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት  በስፋት የታሰሩት፤ ባለፈው ሐምሌ ወር ሲሆን፤ በማዕከላዊ እስር ቤት ለየብቻቸው ታስረው ግርፋትን ጨምሮ የተለያዩ የሀይል እርምጃዎች እየተወሰዱባቸው እንደሚገኙ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።

በዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የሚመራው ቡድን በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ መምርያ ተገኝቶ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ዜጐች፣ መብቶቻቸው ሕገ መንግሥቱና ሕጉ በሚያዘው መሠረት መከበራቸውንና አለመከበራቸውን መጐብኘቱን ገልጾ፣ በተለይ ከእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ችግር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎችን ማነጋገሩን አስታውቋል::

የተጠርጣሪዎቹን አያያዝ በሚመለከት ቤተሰቦቻቸውና ሌሎች ግለሰቦች በተለያዩ ጊዜያት አቤቱታ አቅርበውለት እንደነበር  ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

እንደ ሪፖርተር ዘገባ ኮሚሽኑ በጉብኝቱ ወቅት ትኩረት ሰጥቶ የወንጀል ምርመራ  ኃላፊዎችን ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ስለዋሉበት ሁኔታ፣ ስለ አያያዛቸው፣ ከቤተሰብና ከጠበቆቻቸው  ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት መጠየቁን ገልጿል::

 

የመምርያው ኃላፊዎች ከኮሚሽኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ከፍርድ ቤት በወጣ የመያዣ ትዕዛዝ መሠረት መሆኑን፣ የተያዙትም ከሥራ ቦታቸው፣ ከቤታቸውና ከመንገድ ላይ እንጂ ከፀሎት ቦታ አለመሆኑን፣ ቁጥራቸውም 30 ብቻ እንደሆነና በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን እንደገለጹለት ኮሚሽኑ ተናግሯል::

በሕጉ መሠረት መሠረታዊ መብቶቻቸው እንደተጠበቁላቸው፣ ከቤተሰብ ጋር በአግባቡ  እንደሚገናኙ፣ በፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎች መጐብኘታቸውን፣ በእምነታቸው መሠረት እንዲፀልዩና  እንዲሰግዱ እንደተፈቀደላቸው፣ የመስገጃ ጊዜ ለመከታተል እንዲያመቻቸው የግድግዳ ሰዓት እንደተገዛላቸው የምርመራ ኃላፊዎቹ  መናገራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ኮሚሽኑ በ አመዛኙ በመግለጫው ላይ የዘረዘራቸው ነጥቦች በወንጀል መርማሪ ፖሊሶቹ የተሰጡትን መረጃዎች መሆኑን ያስተዋሉ የዜናው አንባቢዎች፤ መግለጫው የ አንድ የሰብዓዊ መብት ተቋም ሳይሆን የፖሊስ መግለጫ ይመስላል ብለዋል።

ሌላው ይኸው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ አንድም ጊዜ ሳት ብሎት በመንግሰት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ቀለል ያለ ትችት እንኳ ለመሰንዘር ባለመድፈሩ፤ለኢህአዴግ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ወንጀሎች ሽፋን እንዲሰጥ ተብሎ የተቋቋመ ተቋም ነው የሚል ተቃውሞ በስፋት እየተሰነዘረበት ይገኛል።

ኮሚሽኑ፤እነ አንዷለም አራጌ፣እነ እስክንድር ነጋ፣እነ በቀለ ገርባ፣ እነ ኦልባና ሌሊሳ፣እነ ርዕዮት ዓለሙ፣እነ ውብሸት ታዬ እና ሌሎችም በርካታ ዜጎች በታሰሩበት ጊዜ  በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ጉብኝት ካደረገ በሁዋላ ከ አሁኑ ጋር ተመሣሳይ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል።

ከወራት በፊት በፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርብም በ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን ለማሻሻል በተለያዩ ቦታዎች እየተሰጡ ናቸው ባላቸው ስልጠናዎችና ሲምፖለዚየሞች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉ አይዘነጋም።

ወቅቱ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንትን ጨምሮ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በ ኢትዮጵያ እየተፈጸመ ነው ስላሉት መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርታቸውን ይፋ ያደረጉበት ጊዜ ቢሆንም፤ በአምባሳደር ጥሩነህ የሚመራው ኮሚሸን

ስለሰብዓዊ መብት ጥሰት አንዲትም ነጥብ ሳያነሳ ማለፉ ብዙዎችን ያስገረመ ክስተት ሆኖ አልፏል።

በኢትዮጵያ ዜጎች ያለ አግባብ ይታሰራሉ ወይ? ይገረፋሉ ወይ? ይገደላሉ ወይ? በምን ያህል ዜጎች ላይ ህገ-ወጥ እስር ተፈጽሟል? ምን ያህል ሰዎች ያለፍርድ ታስረዋል? እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች በኮሚሽኑ ሪፖርት የማይሞከሩ ነጥቦች ናቸው።

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከበጀታቸው ከ10 በመቶ በላይ ከውጪ ድጋፍ ማግኘት እንደማይችሉ በተደነገገበት በ አሁኑ ጊዜ  በመንግስት ድጋፍ ከተለያዩ ዓለማቀፋዊ ተቋማት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንዲያጋብስ የተፈቀደለት ይኸው ኮሚሽን፤ በገንዘቡ ወርክሾፕና ሴሚናር ከማዘጋጀት ውጪ ሁነኛ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ምርመራ አድርጎ አንድም ሪፖርት ማውጣት አልቻለም።

በአንፃሩ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች በወጣው አዋጅ አቅሙ ክፉኛ እንዲዳከም የተደረገው የቀድሞው የ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) የአሁኑ ሰመጉ ያለችውን ውስን በጀት በማብቃቃት እና ያሉትን ጥቂት ሠራተኞች በመጠቀም በተለያዩ ክልሎች እየተፈፀሙ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተከታታይ ሪፖርቶች ማውጣቱ ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide