የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ኢቲቪን ፦”የቆሻሻ ፕሮፓጋንዳ ፋብሪካ” ሲል ገለጸው

ጥቅምት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት  ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ ሰሎሞን መንግስት  በውሸት ፕሮፓጋንዳ በመማረሩ ሥራውን በፈቃዱ መልቀቁን አስታወቀ።

ጋዜጠኛ ሰሎሞን  መንግስት ባለፉት ዓመታት  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእንግሊዝኛው ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ በመሆን የተለያዩ ዘገባዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል።

በእንግሊዝኛው ፕሮግራም  የተሻለ አቅም ካላቸው ጋዜጠኞች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት  ጋዜጠኛ ሰሎሞን ፤በድርጅቱ የ ኢዲቶሪያል ነፃነት አለመኖሩና ጋዜጠኞች ዘወትር ፕሮፓጋንዳ እንዲሠሩ መታዘዛቸው  ትክክለኛ የጋዜጠኝነት ሙያን እንዳይወጣ እንቅፋት  እንደፈጠረበት ይታመናል።

ጋዜጠኛ ሰሎሞን በፌስ ቡክ ገጹ ዛሬ  በለጠፈው ጽሁፍ  <<”በቃ ማለት በቃ”ነው ብያለሁ። ዳግም ወደዛ የቆሻሻ ፕሮፓጋንዳ ፋብሪካ ወደሆነው የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ላልመለስ ወስኛለሁ>> ብሏል።

የጋዜጠኛ ሰሎሞንን ውሳኔ አስመልክቶ  በርካታ አስተያዬቶች  እየተሰጡ ነው። በርካታ የፌስ ቡክ ጓደኞቹ፦<ሰሎሞን ታላቅ ውሳኔ ነው። ጀግና ነህ። ውሳኔህን እኛም እንከተላለን።እንኳን ከጨለማ ወጣህ!አምላክ ካንተረ ጋር ይሁን!” በማለት በውሳኔው እንደኮሩ ገልጸውለታል።

ጋዜጠኛ ሰሎሞን በ አሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ይሁን አለያም ወደ ውጪ ይውጣ ለማረጋገጥ አልቻልንም።

በስደት የሚገኘው  ኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር የዛሬ ዓመት ባወጣው መግለጫ  እንዳመለከተው   የግል ፕሬስ ጋዜጠኞችን ሳይጨምር ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስት ሚዲያ ሢሰሩ በተፈጠሩባቸው ችግሮች ሥራቸውን በመልቀቅ ወደ ስደት የሄዱ ጋዜጠኞች አሀዝ ከ 50 በላይ ደርሷል።