ለአራት ሳምንታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ቀጥሎ እንደዋለ አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ከስፍራው ለኢሳት ገለጹ።
ኢሳት ያነጋገራቸው ሙስሊም እንደተናገሩት ሰሞኑን በፌስቡክና በሌሎችም መገናኛ መንገዶች እነደተነገረው፤ በዛሬው እለት አማኞች በታላቁ አንዋር መስጊድ በግዜ በመገኘት የእለቱን ጸሎት ከጨረሱ በሁዋላ፤ አስቀድሞ በታቀደው መሰረት መጀመሪያ ነጭ መሀረቦችን በማውለብለብ፤ ለጥቆም አላሁዋክበር በማለት፤ ድምጻቸው እንዲሰማ እንዲሁም የታሰሩት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባለት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባ በአንዋር መስኪድ አካባቢ ቆመጥ የታጠቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት ፈሰው ምእመናኑን ለማስፈራራት ሞክረው እንደነበር የገለጹት ምንጫችን፤ የእስልምናው ምእመን ጸሎቱንም ተቃውሞውንም በሰላማዊ መንገድ አሰምቶ ያለምንም ግጭት ወደየቤቱ እንደተበተነ ገልጸዋል።
እኚሁ ምንጫችን፤ ከመጪው መስከረም 21 ቀን ጀምሮ ይካሄዳል ለተባለው በመንግስት የሚደገፍ የመጅሊስ ምርጫ ሙስሊሙ በግዴታ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ በተለያየ መልኩ እየተገደደ መሆኑን ገልጸዋል።
የቀበሌ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩትን ከቤታችሁ ትባረራላችሁ በሚል ማስፈራሪያ፤ የመንግስት ሰራተኞችንም ከስራቸው ጋር በተያያዘ ጫና በመፍጠር፤ እንዲሁም፤ በቀበሌዎች፤ በወረዳ መስተዳድሮችና በክፍለ-ከተማዎች፤ በሌሎችም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጉዳይ ያላቸውን ጉዳያቸውን በማጓተትና እንደማይፈጸም በማስፈራራት፤ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ እያስገደዷቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
በደሴም በተመሳሳይ መልኩ አንድ መስኪድ በፖሊስ ተከቦ የአካባቢው ሙስሊም ገብቶ እንዳይሰግድ ቢሞከርም፤ ሕዝበ ሙስሊሙ ገፍቶ በመግባት ሳምንታዊውን የጁማ ጸሎት እንዳደረገ ምንጮቻችን ጠቅሰዋል።
በረመዳን ወቅት በደሴ ሙስሊሞች ላይ ፖሊስ ያደረሰውን ድብደባ የሚያሳይ ፊልም በትናንትና ዜና እወጃችን ማሳየታችን ይታወሳል።
ባለፈው አመት ታህሳስ ላይ የተጀመረው የሙስሊሞቹ ነጻ የመጅሊስ ምርጫ ይኑርና በመንግስት የሚደገፈው የአህባሽ አስተምህሮት ይቁም እንቅስቃሴ ተከትሎ፤ ባለፈው ሀምሌ ወር አጋማሽ ብዙ የሙስሊሙ አስተባባሪዎች መታሰራቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የአቶ መለስ ሞት በተነገረበት ሰሞን በእስር ቤት ሰቆቃና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ቤተሰቦቻቸው መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
እስረኞቹ ባለፈው ረቡእ ፍርድቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን፤ ፖሊስ ምርመራዬን አልጨረስኩም በሚል ሰበብ ተጨማሪ ቀጠሮ ጠይቆባቸው፤ ፍርድቤቱ የፖሊስን ጥያቄ ተቀብሎ እስረኞቹ ለመጪው ጥቅምት ሁለት እንዲቀርቡ አዟል።